ከቡና ገለፈት የሚዘጋጅ ሥነ ህይወታዊ የአፈር ማዳበሪያ ፕሮጀክት ሥራ ጀመረ

ዲየ፤ ታህሣሥ 08 ቀን 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተሰራውና በጌድኦ ዞን ወናጎ ወረዳ ቱማታ ጪርቻና በአባያ ወረዳ የተጀመረው ከቡና ገለፈት የሚዘጋጅ ሥነ ህይወታዊ የአፈር ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስ) ፕሮጀክት ሥራ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተካሂዶ ፕሮጀክቶ በይፋ ሥራ ጀመረ፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ በቡና ምርታቸው ከታወቁት ሀገራት አንዷ ስትሆን ቡና ተረፈ ምርት ላይ ሳታውል መቆየተዋን ያነሱት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ ይህ አካባቢን እየበከለ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጥ የቆየውን የቡና ገለፈት በአሁኑ ሰዓት በቨርሚ ኮምፖስ አገልግሎት ላይ እንዲውል መደረጉ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጌድኦ ዞንና የአባያ ወረዳዎች የመሬት ለምነት ከዓመት ዓመት እየቀነሰ መምጣቱን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ይህ ከቡና ገለፈት የሚዘጋጀው ሥነ ህይወታዊ የአፈር ማዳበሪያ (ቨርሚ ኮምፖስ) የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡
የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍሬህይወት እንዳለ በበኩላቸው የዚህ አይነቱ ምርምር በአይነቱ በተቋማችን አዲስ በመሆኑ ተመራማሪዎችንም ሆነ ድጋፍ የሚሰጠውን ክፍል ያለፋና አስቸጋሪ ቢሆንም ውጤቱ እጅግ አመሪቂና አበረታች ነው፤ ብለዋል፡፡
የዚህ ዓይነቱ ምርምር በየወረዳዎች ለማደረስ ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልፅወ ይህን ምርምር ወደ አርሶአደሩ ለማድረስ እያንዳንዱ የመንግስት አካል እገዛ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡
ይህ ምርምር በ21 ቀናት ለአርሶ አደሩ የሚደርስ ነው ያሉት የምርምሩ አስተባባሪ መ/ር ተመስገን ከበደ በአለፉት ጊዜያት ኮምፖስት ለማዘጋጀት ወቅት 3-4 ወር የሚፈጅ ሲሆን ይህ በአጭር ጊዜ ደርሶ የአርሶ አደሩን ችግር የሚቀረፍ ነው፤ ብለዋል፡፡
አቶ ተመስገን አክለውም፣ “አሁን ላይ እየታየ ያለውን የመሬት ለምነት ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ይለውጣል” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የዚህ የማዳበሪያ ዝግጅት ከቨርሚ ኮምፖስት ተረፈ ምርት ዶሮ ማርባት የአርሶ አደሩን ህወት መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ከሁለቱም ወረዳዎች የተጋበዙት የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢ ማህረሰብ እያደረገ ያለው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝና በቀጣይ ወደ በሌሎች ቦታዎች የምርምር ስራዎች ተደራሽ ሊሆኑ ይገባል፤ ብለዋል፡፡
የተጀመሩትም የምርምር ስራዎች ላይ ልዩ ትኩረት ተደርጎ ድጋፉ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሸለ እንዲሆን አስተያየታቸውን አቅርበዋል፡፡