ለ2013 አዲስ ገቢ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ ፕሮግራም ተካሄደ፡፡

ዲ/ዩ ሐምሌ 2/2013 ዓ.ም (ሕ.ግ) እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት የፍሬሽማን ፕሮግራም ማስተባበሪያ ዲን ዶ/ር አስናቀ ይማም ዲላ ዩኒቨርሲቲ እናንተን ለመቀበል ማናቸውንም ዝግጅት አጠናቆ የቆየ በመሆኑ በቆይታችሁ የሰመረ ጊዜ ይኖራችኋል ብለዋል፡፡
በኮቪድ 19 ምክንያት የተራዘመው የናንተ ቅበላ እነሆ ዛሬ ኮቪድ ጠፍቶ ሳይሆን በመከላከል መማር ማስተማር ስራዎችን ማስቀጠል እንዳለብን በማመን ነው ያሉን ዶ/ር አስናቀ በዩኒቨርሲቲው ቆይታችው ወቅት የዩኒቨርሲቲውን መመሪያና ደንብ በማክበር ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አደራ ጭምር አስተላልፈዋል፡፡
የተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ጌካ በበኩላቸው በተማረዎቹ ቅበላ ወቅት የተማሪዎች ክበባትና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው አካላት ተማሪዎቹን ተቀብሎ እስከ ዶርማቸው ለማድረስ ያደረጉትን ጥረት አድንቀው ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው በሚቆዩበት ወቅት በካፌ፣ በህክምናና ተዛማች የሆኑ አገልግሎቶችን ለመጠቀም የሚሰጣቸውን ID Card በአግባቡ በመያዝ እንዲጠቀሙና ማንኛውንም አገልግሎት ማግኘት የሚቻለው በተሰጠው ጊዜ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሬጅስትራልና አልሙናይ ም/ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በበኩላቸው ለተማሪዎቹ ከቅበላ እስከ ምረቃ ድረስ አብሮነታቸውን ገልፀው በዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ካላንደር መሰረት የመማር ማስተማር ሂደቱን በመከታተል የተሻለ ውጤት የሚያስመዘግቡ ምሩቃን እንደሚሆኑ ባለሙሉ እምነት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ለ2013 የትምህርት ዓመት 2998 ሴት እና 1934 ወንድ በድምሩ 4932 ተማሪዎችን ዲላ ዩኒቨርሲቲ መቀበሉ ይታወቃል፡፡