የዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን 3468 ተማሪዎች በታላቅ ድምቀት አስመረቀ።

ዲ.ዩ ነሐሴ 2 ቀን 2013 ዓ.ም (ህ.ግ) አገራችን በተለያዩ ሁኔታዎች እየተፈተነች ባለችበት በዚህ ወቅት ተግታችሁ በመስራት ዛሬ ላይ ይህቺን ቀን ስላያችሁ በራሴና በቦርዱ ስም እንኳን ደስ ያላችሁ ያሉት የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዲሪ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አዱኛ ደበላ በእድገት ጎዳና ላይ ያለች አገራችንን ወደ ከፍታ ማማ ለማውጣት የእናንተ የእያንዳዳችሁ አሻራ ያስፈልጋታልና ያስተማረች አገራችሁን እያሰባችሁ በርትታችሁ እንድትሰሩ አደራ እላለሁ ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ችሎታው አየለ በበኩላቸው በአገራችን በኮቪድ 19 ምክንያት ለ1 ዓመት ትምህርት ቢቋረጥም በተለየ ሁኔታ የትምህርት መርሀ ግብር ወጥቶ ትምህርታችሁን ጨርሳችሁ ለዚህ ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ዶ/ር ችሮታው አያይዘውም የአገራችንን ዕድገት ለማፋጠን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በተለየ ተልዕኮ አዲስ ፍኖተ ካርታ በተዘጋጀላቸው መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ የአፕላይድ ሳይንስ ዩንቨርሲቲ ሆኖ በመመደቡ ከወትሮው በተጠናከረ መልኩ የተግባር ተኮር ትምህርት በመስጠት ላይ እንገናኛለን ብለዋል።
የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የዲላ ዩንቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው ተመራቂዎች የተለያዩ ፈተናዎችን በማለፍ ለዚህ ትልቅ ድል በመብቃታቸው የተሰማቸውን ላቅ ያለ ደስታ ገልፀው ሀገራችን የገጠማትን የውስጥና የውጪ ጣልቃ ገብነት ፈተናዎችን ድል ለመንሳት በጋራ ቆመን የኢትዮጵያን ዘላቂ ብልፅግና የምናረጋግጥበት ወቅት ነው ብለዋል::
ያነጋገርናቸው በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆኑ ተማሪዎች ይህን የላቀ ውጤት ሊያመጡ የቻሉት በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ዕለት ተዕለት ተግተው በመስራታቸው እንደሆነ ገልፀውልናል።
ለ23ኛ ዙር ዛሬ የዲላ ዩንቨርሲቲ ያስመረቃቸው ተማሪዎች በመጀመሪያ ዲግሪ 3084 በሁለተኛ ዲግሪ 384 በደምሩ 3468 ተማሪዎች ሲሆኑ በ1989 ዓ.ም. መማር ማስተማሩን ከጀመረበት አንስቶ ከ71,000 በላይ ምሩቃንን በማፍራት ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል::