በዲላ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የአትክልት ችግኝ ስርጭት ተካሄደ።

ዲ.ዩ ነሐሴ 21ቀን 2013 ዓ.ም. (ሕ.ግ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ በጎላ፣ ሲሶታ፣ አንዲዳና ጪጩ ቀበሌዎች ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫና የአትክልት ችግኝ ስርጭት አካሄደ። 

የግንዛቤ ማስጨበጫው ዋና ዓላማ አርሶ አደሩ በአትክልት ችግኝ አተካከል ዙሪያ በቂ ዕውቀት ኖሮት የአትክልት ምርቶችን በዘላቂነት እንዲያቀርብ በማስቻል ማህበረሰቡ በአካባቢው በመገንባት ላይ ላለው ኢንዱስትሪ ፓርክ  የአትክልትና ፍራፍሬ ግብአት እንዲያቀርብ ለማስቻል መሆኑን የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጽ/ቤት አሳውቋል። 

በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሆርቲካልቸር ትምህርት ክፍል መምህርና የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኝ ፕሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ፍቅሩ ታምሩ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በአካባቢው ይመረቱ የነበሩት ፍራፍሬዎች በመጠንም ሆነ በምርታማነት ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር ያነሰ ውጤታማነት እንደነበራቸው ገልጸው አሁን ላይ ግን ለተከላ የተሰራጨው ምርጥ ዘር በአገሪቱ ደረጃ በመልካሳ ግብርና ምርምር ማዕከል ምርታማነታቸውና ጣዕማቸው ጥሩ መሆኑ ተረጋግጦ የተለቀቁ በመሆናቸው ችግኞቹ ተገቢውን እንክብካቤ ከተደረገላቸው አርሶ አደሩን ይበልጥ ትርፋማና ውጤታማ እንዲሆን  የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል። 

አስተባባሪው አያይዘውም በቀጣይ አርሶ አደሩ በራሱ ችግኞችን አፍልቶ መጠቀም እንዲችል የተለያዩ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።