የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሪፈራል ሆስፒታል ሴት ሠራተኞች ፎረም ተመሠረተ፡፡

ዲ.ዩ ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) የአንድን ሀገር ዜጎች እኩል ማየትና ለፆታ እኩልነት ቦታ መስጠት ያስፈልጋል ያሉን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሪፈራል ሆስፒታል ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሠላማዊት አየለ በሀገራችን አንቱ የተባሉ በርካታ ስራዎችን የሰሩ ሴት አመራሮች መኖራቸውን አውስተው ሴቶች በአንድነት በመሆን ሲታገሉም ሆነ ለመብታቸው ሲሰሩ ለውጥ ማምጣት ይችላሉ ብለዋል፡፡

ይህ ፎረም ዛሬ በጤና ሳይንስ ኮሌጅና ሪፈራል ሆስፒታል ባሉ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞች፣ የጤና ባለሙያዎችና የስርዓተ ፆታ ኃላፊዎች ተገኝተው የተመሰረተ መሆኑንም ዶ/ር ሠላማዊት ተናግረዋል፡፡

በፎረሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ወ/ሮ የምስራች ገመዴ የደቡብ ክልል ሴ/ህ/ወ/ጉዳይ ም/ኃላፊ እና ወ/ሮ ሙሉሸዋ መኮንን የዲላ ከተማ የወላጅ አልባ ህፃናት አሳዳጊ ድርጅት መስራችና ኃላፊ እንደተናገሩት ይህ የሴቶች ፎረም መመስረቱ በሆስፒታላችን ያሉ ሴቶች የአመራርነት አርአያነት ለሌላዋ ሴት ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ይህ ፎረም በአሁኑ ሰዓት በክልል ደረጃ ሊቋቋም ታስቦ እንደነበር የተናገሩት ወ/ሮ የምስራች እናንተ መቅደማችሁ ፎረሙን መመስረታችሁ እጅግ የሚያስደስትና ያላችሁን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በፎረሙም ላይ በመምህርት ፍሬህይወት በላይነህ “ሴቶች እና አመራርነት” በሚል ርዕሰ-ጉዳይ የውይይት ጽሑፍ ቀርቧል:: ጽሑፉም በወናነት በሴት ልጅ ተፈጥሮአዊ የአመራር ባህርያት እና ሴቶች ወደ አመራርነት እንዳይመጡ ተግዳሮት የሆኑ ጉዳዮችን ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን ሰፊ ውይይት በጉዳዩና በመፍትሄ ሃሳቦች ዙሪያ ተደርጓል፡፡

በተጨማሪም በአመራርነት ዘመናቸው ለሴቶች አራአያ ለሆኑት ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የሪፈራል ሆስፒታል ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሠላማዊት አየለ የእውቅና ሰርተፍኬትና የአንገት ሀብል ሽልማት መሰጠቱን ለማወቅ ችለናል፡፡

ከሽልማቱ በኋላ ያነጋገርናቸው ዶ/ር ሠላማዊት አየለ ይህ ሽልማት ያልጠበቁትና ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ለሚሰሩት ስራ ትልቅ እገዛ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ 

በምርምር ዘርፍ አንቱ የተባለ ስራ የሰሩት መምህርት ደራርቱ ነሜ በዘንድሮ ዓመት ሞሼ ባዘጋጀው የሀርት ኮንቬንሽን (HEART Convention) ላይ አሸናፊ ሆና ዩኒቨርሲቲያችንን ያስጠራች በመሆኗ የእውቅና ሰርተፍኬትና የ5 (አምስት) ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡   በውይይቱ ማጠቃለያ ላይም የሴት ሠራተኞች ፎረም አስተባባሪ ኮሚቴዎችን በሰራተኞች ጥቆማ መሠረት ምርጫ በማካሄድና በማፅናት ዝግጀቱ ተጠናቋል፡፡