ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሲያካሂድ የነበረዉ የመጀመሪያው ሀገር ዓቀፍ የSTEAM Research ኮንፍረንስ ተጠናቀቀ፡፡

ዲ.ዪ ጥቅምት 20/2014 ዓ/ም /ህ.ግ/ STEAM ማዕከል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ሆነ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረዉ በቅርብ ጊዜ ነዉ ያሉት ዶ/ር ዳዊት ሃዬሶ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስ/ተማ/አገ/ምክ/ፕሬዚዳንት እና የፕሬዝዳንቱ ተወካይ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያሳየን STEAM ላይ ጠንካራ ስራ መስራታቸዉ አሁን ላሉበት የእድገት ደረጃ እንዲደርሱ ከፍተኛ ሚና እነደነበረዉ ጠቅሰዉ እኛም ሀገራችንን ከድህነት እና ኋላ ቀርነት ለማላቀቅ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እዉቀትና ክህሎት የታነጸ ትዉልድ ማፍራት ለነገ የማይባል ስራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ STEM ማዕከል የተመሰረተዉ ከ8 ዓመት በፊት እንደሆነ የገለጹት ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ተክ/ሽግ/ምክ/ፕሬዚዳንት ተወካይ ማዕከሉ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተወዳዳሪ እና ብቁ ዜጋ ለማፍራት በአካባቢዉ ከሚገኙ ወረዳዎች የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች ተወዳድረዉ አመርቂ ዉጤት ያመጡ እና ለፈጠራ ስራ ዝንባሌ ያላቸዉ ተማሪዎች በክረምት ፕሮግራም እየተቀበለ እስከ ዘንድሮ 2457 ተማሪዎች አስልጥኖ ማስመረቁን አሳውቀዋል፡፡
ስልጠና ያገኙ ተማሪዎች የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች እንደሰሩ በዚህ ኮንፈረንስም ስራቸዉን ለታዳሚዎች እይታ እንዳቀረቡና በሀገር ዓቀፍ ደረጃ ተወዳድረዉ ለሽልማት የበቁ እንዳሉ አክለዉ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር አብርሃም ዓለማየሁ በትምህርተ ሚኒስቴር የSTEAM ማዕከል ዳይሬክተር በበኩላቸዉ ትምህርት ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት ከ1ኛ ደረጃ ጀምሮ ተማሪዎች የተግባር ትምህርት ከሥነ-ሃሳብ ትምህርት ተጣጥሞ እንዲሄድና እና አመርቂ ዉጤት እንዲመጣ በትምህርት ካሪኩለም እና ፖሊሲ እንዲደገፍ ሰፊ ስራ እየተሰራ እነደሆነ ገልፀዋል፡፡
ከአጸደ ህፃናት ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ለሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ትምህርት የስልጠና እድል እንዲያገኙ ከዪኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እንሰራለን ያሉት ዶ/ር ስሜነዉ ቀስቅስ የSTEM Power ዳይሬክተር ተቋማቸዉ በአሜሪካ ሀገር የተመሰረተ ግብረ ሠናይ ድርጅት ቢሆንም በብዛት ስራ የሚሰራዉ በኢትዮጵያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ዋና ዓላማቸዉ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ለልጆች የተግባር ተኮር የትምህርት ስልጠና ዕድል እንዲያገኙ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በኮንፍረንሱ መጨረሻም የጥናት ጽሁፍ አቅራቢዎች÷ የኮንፍራንሱ ታዳሚዎች አና የግቢዉ ማህበረሰብ አባላት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርጥ ቡና ዘር ችግኝ ማፍያ ሳይት÷ የሞዴል አርሶ አደር የቡና ማሳ÷ ጨላባ ቱቲቲ ትክል ድንጋይ እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ እጽዋት እንክብካቤ እና ኢኮ-ቱሪዝም ማዕከል በመጎብኘት ፕሮግራሙ ተጠናቅቋል፡፡