የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር አብሮ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ዲዩ ህዳር 02/2014 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነት) ተቋማችን ከአፕላይድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተመደበ በመሆኑ በተግባር ትምህርት እጃቸውን የፈቱ ሙሩቃንን ለማፍራት ቆርጦ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ደረጀ ክፍሌ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምር/ቴክ/ሽግ/ምክ/ፕሬዝዳንት ተወካይ ከተቋማት ጋር የሚኖረን ትስስር በእጅጉ የጠበቀ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ስርዓተ ትምህርት ሲቀረፅ የኢንዲስትሪዎችን ፍላጎት ያገናዘበ እንዳልነበረ ተናግረው አሁን ላይ ከተለያዩ ፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች ፍላጎት እና የስራ እድል ከማስገኘት አኳያ ስርዓተ ትምህርት እየተቀረፀ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ደረጀ አክለውም የደቡብ ሬድዮና ቴሌቭዝን ድርጅት ባለው ቴክኖሎጂ በመታገዝ እኛጋ ያለውን ዕውቀት በማስተሳሰር በክህሎቱ የተሻለ ዜጋ ለመፍጠር ይህን የመሰለ ስምምነት መፍጠራችን እገዛው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የደቡብ ፌድዮና ቴሌቪዥን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሀብቴ በበኩላቸው እኛ ወደ እናንተ መምጣት ሲገባን እናንተ ወደኛ መታችሁ ይህን የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም መብቃታችን ተቋሙ ምን ያህል ቁርጣኛ አቋም ይዞ ስራ እየሰራ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በሀገራችን ካሉ ሚዲያዎች መካከል የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በ48 የብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋ በ8 ቅርንጫፍ ጣቢያዎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለው ከዚህ በፊትም ከዲላ ዩንቨርስቲ ጋር በርካታ ስራዎችን እየሰራን ያለን ቢሆንም ይህ የመግባቢያ ሰነድ ሥራዎቻችንን ለማተለቅ ትልቅ እገዛ አለው ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት የራሳቸው አቅም ያላቸው በመሆናቸው በቀጣይ ለተማሪዉም ሆነ ለማህበረሰቡ ትልቅ ጉልበት ይሆናሉ ብለዋል፡፡

ይህ የመግባቢያ ስምምነት ረጅም ግዜ የፈጀ ሀሳብ እንደነበር የገለፁልን አቶ አሻግሬ ተሾመ የእስትራቴጅክ ስራ አመራርና የሚዲያ ጥራት ኃላፊ ዛሬ ለመፈራረም የበቃነውን የመግባቢያ ሰነድ በሁለቱም ተቋማት መፈራረም ብቻ ሳይሆን ወደ ስራ በመግባት ለሀገር የሚበጅ ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡