ዲ.ዩ፤ ጥር 25/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2015 ዓ.ም የትምህርት ዘመን በተሰጠው የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ኮሌጆች እና ትምህርት ክፍሎች እውቅና መሰጠቱ ተገልጿል።
ማቲዎስ ሀብቴ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ፕሮግራሞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ እንደ ሀገር የትምህርት ጥራትን ለማሻሻልና ለማስጠበቅ ከተጀመሩት ለውጦች አንዱ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለእጩ ምሩቃን የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና መስጠት መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ 1,682 ተማሪዎቹን እንዲሁም 1,096 በዲላ ከተማና አካባቢው የሚገኙ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን በአጠቃላይ 2,782 ተማሪዎችን በ2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና ማስፈተኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ማቲዎስ፤ ፈተናውን በስኬት ለማጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዳደረጉ አስታውሰው፤ በዚህም ዩኒቨርሲቲው 72.34 ከመቶ የማሳለፍ ምጣኔ ማስመዝገቡን ገልጸዋል። በዚህም የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ያስፈተናቸውን ተማሪዎች 94.3 በመቶ በማሳለፍ አመርቂ ውጤት በማስመዝገቡ የዋንጫ እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሸላሚ ሲሆን፤ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ ሰብዕ ኮሌጅ ያስፈተናቸውን ተማሪዎች 87.2 በመቶ በማሳለፉ እንዲሁም የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ ካስፈተናቸው ተማሪዎች 80.8 በመቶ የማሳለፍ ምጣኔ በማስመዝገብ የእውቅና የምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
በትምህርት ክፍል ደረጃ ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ (100%) በማሳለፋቸው የጋዜጠኝነትና ሥነ-ተግባቦት፣ የአፋን ኦሮሞ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ እንዲሁም የጌዴኡፋ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ክፍሎች የእውቅና ምስክር ወረቀት አግኝተዋል።
የእውቅና ሽልማቱ ዓላማ ኮሌጆችንም ሆኑ የትምህርት ክፍሎችን ላስመዘገቡት አርኪ ውጤት ለማመስገንና ለቀጣይ ስራዎች የተነሳሽነት እና የኃላፊነት ስሜት ለመፍጠር እንደሆነ ዶ/ር ማቲዎስ አስገንዝበዋል።
ሳምሶን ኃ/ማርያም (ዶ/ር)፣ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ተወካይ ዲን፤ ኮሌጃቸው እንደ ተቋም የተሻለ ውጤት በማስመዝገቡ የዋንጫ ተሸላሚ በመሆኑና የእውቅና የምስክር ወረቀት በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ ይህ ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኃላፊዎችና መምህራንን አመስግነዋል።
ይህንን ስኬት ለማስቀጠልም ከወዲሁ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ዶ/ር ሳምሶን አያይዘው ገልጸዋል።
ኢዮብ ቀለመወርቅ (ዶ/ር)፣ የማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብዕ ኮሌጅ ዲን በበኩላቸው፤ እንደ ተቋም ያስፈተኗቸውን ተማሪዎች ሙሉ ለሙሉ በማሳለፍ የእውቅና የምስክር ወረቀት ያገኙት ሶስቱም ትምህርት ክፍሎች በማሕበራዊ ሳይንስና ሥነ ሰብዕ ኮሌጅ ስር የሚገኙ መሆናቸውን አስታውሰው፤ ኮሌጁ ያስፈተናቸውን ተማሪዎች 87.2 በመቶ ለማሳለፉ የመምህራን፣ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ የኮሌጅ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጥረት ከፍተኛ እንደነበር ገልጸው፤ የኮሌጁ አባላት እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
እንደ ኮሌጅ በቀጣይ ለሚሰጠው የመውጫ ፈተና ከዚህ በተሻለ ስኬት ለማጠናቀቅ ዕቅድ በመንደፍ ወደ ተግባር እንደተገባ ዶ/ር ኢዮብ አክለው ገልጸዋል።
በ2015 ዓ.ም የመውጫ ፈተና የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡት ኮሌጆችና ትምህርት ክፍሎችም የእውቅና የምስክር ወረቀቱን ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እና ከአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታምራት በየነ እጅ ተቀብለዋል።