ዲ.ዩ፤ ግንቦት 28/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውን ምሁር በመጋበዝ በዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ጉድኝት ዙርያ የህዝብ ዲስኩር (Public Lecture) እንዲሰጡ ማድረጉ ተገልጿል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲዎች ሲቋቋሙ አካዳሚክና የምርምር ስራዎች ብቻ ይዘው የተቋቋሙ በመሆናቸው የማህበረሰብ አጋርነት ላይ ትኩረት ያላደረገ እንደነበር አውስተው፤ አሁን ላይ ማህበረሰብና ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ጉድኝት በመፍጠርና አብረው በመስራት የህብረተሰቡን ችግር መፍታት የሚችሉበት ሁኔታ ላይ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
እንደ ዶ/ር ሀብታሙ ገለጻ፤ በማህበረሰብ አገልግሎት ዙርያ ሰፊ ስራ የተሰራ ቢሆንም ወደ ማህበረሰብ ተሳትፎ ያልተገባ በመሆኑ ማህበረሰብ ውስጥ ያለውን ሀብት (እውቀት) በማስተሳሰር ከማህበረሰቡ አካባቢ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ጉድኝት ውስጥ በማካተት በመስራት እጁን ያፍታታ ትውልድ ማፍራት ይቻላል።
የእለቱን የህዝብ ዲስኩር ያቀረቡት ኘሮፌሰር አሰፉ ገ/አምላክ ከአሜሪካ ኮሎራዶ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሲሰሩ የነበሩና አሁን ላይ ‘ፊዲ ብራይት’ በሚል ኘሮግራም በኢትዮጵያ ውስጥ የማህበረሰብ ተሳትፎን መሰረት አድርገው እየሰሩ ያሉ ምሁር ሲሆኑ እንደ ፕሮፌሰር አሰፋ ገለጻ፤ የዩኒቨርሲቲ ጉድኝት ዩኒቨርሲቲዎች ላሉበት ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን በጠቅላላው ለሀገሪቷ ከሚሰጡት አስተዋጽኦ ባለፈ ማህበረሰቡ ጋር ምን አቅም አለ የሚለውን በመለየት ከማህበረሰቡ ጋር በጋራ የሚሰራበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሆነ አስረድተዋል።
ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች የብቃት ችግር የሚነሳባቸውና ችግር ፈቺ አይደሉም የሚባሉት ምክንያቱ የትምህርት አሰጣጡ ተግባር ተኮር አለመሆንና የማህበረሰብ ጉድኝት ላይ ያልተመሰረተ በመሆኑ ነው ሲሉ ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት ዳሬክተር አቶ ተካልኝ ታደስ በበኩላቸው፤ የማህበረሰብ አገልግሎት እንደ አገር ያለውን ተሞክሮ በመውሰድ ወደ ማህበረሰብ ጉድኝት እሳቤ መለወጡን ገልጸው፤ ባለፉት ጊዚያት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ መምህራን ብቻ ያሳተፈ እንደነበር በማንሳት አሁን ተማሪዎችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻዎች ሁሉ ተሳትፈውበት በጋራ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር አብሮ የመፍታት ሂደት እንደሆነ ገልጸዋል።
ፐብሊክ ዲስኩሩን ሲከታተሉ ካገኘናቸው ተሳታፊዎች መካከል አብዮት መብራቴ (ዶ/ር) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሀገረሰብ ጥናት ተቋም ዳሬክተር፤ የዩኒቨርሲቲ-ማህበረሰብ ጉድኝት ዩኒቨርሲቲውን እና ማህበረሰቡን በጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ እርስ በእርስ የሚያስተሳስር መሆኑ በዚህ ሂደት የተሻለ የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ከዲላ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የመጡት አቶ ተስፋልደት ማርቆስ በበኩላቸው፤ ተመራቂ ተማሪዎች ተመርቀው ወደ ማህበረሰቡ ከመቀላቀላቸው በፊት በተግባር ማህበረሰብ ውስጥ መስራታቸው እጃቸውንም ሆነ አእምሮአቸውን አብቅተው ወደ መጡበት አካባቢ ሲሄዱ ችግር እንዳይገጥማቸው እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et