ዲ.ዩ፤ ግንቦት 15/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ከጌዴኦ ዞን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለተውጣጡ የኬምስትሪ መምህራን “በኬሚስትሪ ቨርቹዋል ቤተ ሙከራ” ዙሪያ በዲላ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ለአራት ተከታታይ ቀናት ተግባር ተኮር ስልጠና ተሰጥቷል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ አቶ ዘማች ክፍሌ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ በአገራችን በብዙ ጥናቶች ጭምር እንደተረጋገጠው 60% እና ከዚያ በላይ የሆነ ተማሪዎች ውጤት በመማር ማስተማር ላይ ጥገኛ የሆነ እንደመሆኑ በሀገሪቱ የተቀረፀውን ስርዓተ ትምህርት በትክክል ለመተግበር እና የትምህርት ስብራቱን ለመጠገን ከተማሪው ባለፈ የመምህራንንም አቅም ማሳደግ ወሳኝነት ያለው በመሆኑ ስልጠናው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
አቶ ዘማች አያይዘውም፤ እንደዚህ ያሉ ስልጠናዎች በዞኑ በራሱ የሚተማመን እንዲሁም ትውልድን የሚገነባ ብቁ መምህር ለመፍጠር ትልቅ አቅም እና መነሳሽ የሚሆኑ በመሆናቸው መምህራን ስልጠናውን በአግባቡ በመከታተል ሙያዊ ዕውቀታቸውን ማሳደግ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል
አቶ ፈጠነ ባሌሲ፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት የስልጠናና ማማከር ኦፊሰር፤ ስልጠናው የዞኑ ትምህርት መምሪያ ጽ/ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ የመምሪያውን ፍላጎት መሰረት ባደረገ መልኩ ከዞኑ ለተውጣጡ 26 ወንድ እና 4 ሴት በጠቅላለው 30 ለሚደርሱ የሁለተኛ ደረጃ የኬሚስትሪ መምህራን መሰጠቱን ገልጸዋል ።
አቶ ፈጠነ አያይዘውም ፤ በቀጣይ እንደ ዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ስልጠናዎችን ከመስጠት ባለፈ የተሰጡ ስልጠናዎች በማህበረሰቡም ይሁን በተቋማት ምን አይነት ለውጥ አመጡ፣ የትኞቹስ ተግባራዊ ሆኑ የሚሉትን ነገሮች ከክትትል ከማድረግም ባለፈ ጥናትም ጭምር ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ መሆናኑን ተናግረዋል።
ከአሰልጣኞች መካከል በዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጅ በኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል የፊዚካል ኬሚስትሪ መምህር፣ ብርሃኑ ወንዴ በበኩላቸው፤ ይህ ስልጠና መምህራኑ ከስልጠናው በኃላ ሶፍትዌሮችን በመውሰድ ምንም አይነት የኬሚካል ግዥዎች ሳይፈጸሙ እና የላብራቶሪ ዕቃዎችን ሳይጠቀሙ ያለምንም ስጋት ኮምፒውተሮችን ብቻ ተጠቅመው ሳይንሱን ወደ ተግባር የሚለውጡበት ተግባር ተኮር ስልጠና እንደመሆኑ ስልጠናው ለመምህራኑ ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታ ከማስገኘት ባለፈ በሳይንስ ላይ ያላቸውን ዕውቀት አንድ ደረጃ ከፍ እንዲያረጉ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
መምህር ብርሃኑ አያይዘውም፤ ይህ የቨርችዋል ኬሚስትሪ ቤተ ሙከራ ስልጠና ግቡን የሚመታው መምህራን ከስልጠናው በኃላ ወደየመጡበት ሲመለሱ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም የወሰዱትን ስልጠና ተግባራዊ ሲያደርጉ በመሆኑ የትምህርት አመራሮች ስራው ከኮምፒውተር ጋር ተያይዞ የሚሰራ መሆኑን ተረድተው ሰልጣኞቹ ለሚሰሩት የድህረ ስልጠና ተግባራት ኮምፒውተሮችን ዝግጁ በማድረግ እንዲያግዟቸው ጠይቀዋል።
ሰልጣኞቹም ከስልጠናው በኃላ ወደ የመጡበት ሲመለሱ ከዚህ የወሰዷቸውን ሶፍትዌሮች በትምህርት ቤቱ ኮምፒውተሮች ላይ በመጫን ሌሎች መምህራንን ማስልጠን እንዲሁም ተማሪዎችንም ማስተማር እንደሚጠበቅባቸው መ/ር ብርሃኑ አያይዘው ተናግረዋል።
በስልጠናው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ ይህ የቨርቹዋል ኬሚስትሪ የላብራቶሪ ስልጠና በአሁኑ ወቅት በዞኑ የሚገኙ የ2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በኬሚካል እጥረት ምክንያት ለሳይንስ ተማሪዎች ከንድፈ -ሃሳብ ያለፈ የላብራቶሪ የተግባር ትምህርቶችን የማይሰጡ በመሆናቸው ተማሪዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሳይንስ ትምህርት እየሸሹ ስለሆነና በቀጣይም ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ በዞኑ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ላይኖሩ ስለሚችል ይህን ችግር ለመቅረፍ ለተማሪዎች በኬሚካል ሊሰጥ የሚችለውን የላብራቶሪ ስራ መምህራኑ በኮምፒተር እንዲሰጡ ለማስቻል ስልጠናው መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ይህ የቨርቹዋል ኬሚስትሪ ስልጠና የጌዴኦ ዞን በብዛት ቡና አብቃይ ገበሬ ያለበት ስፍራ እንደመሆኑ አካባቢውን ከምንም አይነት ኬሚካል ከመጠበቅ አኳያም ሆነ የአካባቢን ብክለት ከመቀነስ አንፃር ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑ ስልጠናው መምህራኑን ከማብቃትና እና ተማሪዎችን ወደ ሳይንስ ትምህርቶችከመመለስ ባለፈ ዘረፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት እንደሆነ አቶ ተካልኝ አያይዘው ተናግረዋል።
ስልጠናውን ሲሳተፉ ያገኘናቸው ከቡሌ ባሱራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት መምህርት ጀሚላ ከይረዲን፣ እንዲሁም ከዲላ ዳማ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡት መ/ር እንዳልካቸው አሰፋ እንደገለጹት፤ ይህ የቨርችዋል ቤተ ሙከራ ስልጠና ለተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶች ያለኬሚካል በኮምፒውተር ብቻ ለተማሪዎች የተግባር ትምህርት ለመስጠት የሚያስችል በመሆኑ ስልጠናው ለመምህራንም ሆነ ለተማሪዎች ትልቅ አቅምን ብሎም መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በቀጣይ አመትም ይህን የቨርቹዋል ቤተ ሙከራ ስልጠና በተመሳሳይ መልኩ በሌሎች የትምህርት አይነቶች ማለትም በፊዚክስ፣ በባዮሎጂ እና በሒሳብ ትምህርቶች ላይ ለመስጠት እቅድ መያዙ ከአዘጋጆቹ ተገልጿል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et