ዲ.ዩ፤ ጥር 22/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርስቲ መምህራን በተልዕኮ ልየታ (Differentiation) ስትራቴጂ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት አጠቃላይ የትምህርት ስረዓቱን ሪፎርም ለማድረግ ያስችል ዘንድ በተዘጋጀው የትምህርት ፍኖተ ካርታ የትምህርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህም መሰረት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ ዩኒቨርሲቲዎችን በተልዕኮ መለየት በማስፈለጉ በትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲዎች የተልዕኮ ልየታ ተሰርቷል
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ በተሰራው የተልዕኮ ልየታ መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንደ ሀገር ተግባራዊ ዩኒቨርሲቲ (Applied Science University) ሁነው ከተለዩ 15 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ ግብርናን፣ ተፈጥሮ ሀብትን፣ የመምህራን ትምህርትን እና ጤናን የትኩረት መስክ አድርጎ እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል። አክለውም በትምህርት ሚኒስቴር በተላከው የተልዕኮ ልየታ ትግበራ ማንዋል ዙሪያም ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ እስከ ታቸኛው አመራር፣ መምህራንና ሰራተኞች በተለያዩ አደረጃጀት እርከኖች ውይይቶች ሲያደረጉ መቆየታቸውን አስገንዝበዋል። የዛሬው መድረክም ሁሉም መምህራን ከዩኒቨርሲቲው አመራር ጋር በጋራ በተልዕኮ ልየታው ዙሪያ በመወያየትና ሀሳብ በመለዋወጥ የጋራ ስምምነት ይዘው የተጀመረውን ስራ ዳር ለማድረስ እንዲያግዝ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ባቀረቡት የተልዕኮ ልየታ ስትራቴጂ ሰነድ ተማሪዎች በገበያው ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ክህሎት ይዘውና ብቁ ሆነው እንዲወጡ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ስኬታማነትም ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በመቀናጀት በትብብር የተመሰረተ ትምህርት እንደሚሰጥ አስረድተዋል።
ዶ/ር ታምራት ከዚህ ጋር አያይዘውም፤ አለማቀፋዊ ልምዶችን በማንሳት ከአቅም ግንባታ፣ ከስረዓተ ትምህርት ክለሳ እና ከመምህራን ምጥጥን ጋር የተያያዙ መሰረታዊ የሚባሉ ለውጦች እንደሚደረጉ ገልጸዋል። ጥራትን ከማስጠበቅ አንጻር የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም ስረዓተ ትምህርቶች እውቅና እንዲያገኙ እየተሰራ እንደሆነም ተናግረዋል። በአልሙናዮች፣ በአለማቀፋዊነት፣ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ትስስርንና አጋርነት ከመፍጠር እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የሚሰራበትን መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ባቀረቡት ሰነድ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው በምርምር ዘርፍ የተልዕኮ ልየታውን ተተግባሪነት የሚደግፉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ቀድሞውኑ ተዘጋጅተዋል። የዩኒቨርሲቲው ራዕይና ተልዕኮ፣ የምርምር ትኩረቶች (Thematic Areas) የዩኒቨርሲቲውን የትኩረት መስክ መሰረት እንዲያደርጉ ሁነው ተቃኝተዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም፤ አካባቢያዊ ፀጋን በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከማውጣት አንጻር የተለያዩ የዩኒቨርስቲው ተመራማሪዎች በጌዲኦ ዞን የመሬት ገጽታ ላይ ባካሄዱት ምርምር የጌዴኦ መልበዓ ምድር በUNESCO እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል። በትብብር መስራትና አለማቀፋዊነት በተልዕኮ ልየታው ወሳኝ ጉዳዮች ሲሆኑ ለዚህም የተለያዩ ፕሮጄክቶችን አፈላልጎ የሚያመጣ ቡድን (Project Hunting Team) ተቋቁሞ በትብብር ሊሰሩ የሚችሉ ልዩ ልዩ ፕሮጄክቶችን እያመጣ እንደሆነ ዶ/ር ሀብታሙ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ዶ/ር ሀብታሙ በምርምር ውጤቶች የማህበረሰብን ችግር መፍታት፣ ምርምሮችን በተለያዩ ጆርናሎች ማሳተም፣ የፈጠራ ባህል ማሳደግና ማጠናከር በሚቻልባቸው እና ሌሎችም ሐሳቦች ዙሪያ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።
በቀረቡት ጽሁፎች እንዲሁም በተልዕኮ ልየታ ስትራቴጂ ትግበራ ዙሪያ በፕሬዝዳንቱ እና ምክትል ፕሬዚዳንቶች መድረክ መሪነት የተለያዩ ሐሳብና አስተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች ተነስተው ሰፊ ውይይት ተካሂዶባቸዋል። በዚህም በተቋም ደረጃ መሰራትና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ሁሉም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እንዲስተካከሉ እንዲሁም በመንግሥት ደረጃ መፈታት ያለባቸውን ጉዳዮች ለሚመለከተው አካል ምክረ ሀሳብ እንዲቀርብ መግባባት ላይ ተደርሷል።
በመጨረሻም ዶ/ር ችሮታው፤ የልየታ ትግበራውን በተመለከተ በየደረጃው ውይይቶች እየተደረጉ ሃሳብና አስተያየቶች እንዲቀርቡ እንዲሁም ይህንን የሚያስተባብር ዳይሬክቶሬትም እንደሚደራጅ ገልጸዋል። ለዚህ ስኬታማነትም ሁሉም አመራሮች፣ መምህራን እና ሰራተኞች ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም መንግሥትና ተቋሙ የሚያካሂዱትን የለውጥ ስራ በቅንነትና በትጋት በመከወን ለሀገር እድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።