ዲ.ዩ፤ የካቲት 13/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችና በመሰረታዊ የቤተ ሙከራ ጥራት አተገባበር ዙሪያ ከይርጋጨፌ፣ ቡሌና ገደብ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ የጤናና የሕክምና ቤተ ሙከራ ባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን ተገልጿል።
አቶ ትዝለኝ ተስፋዬ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ በስልጠናው መርሃ ግብር ባደረጉት ንግግር ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው ላሉ የጤና ተቋማት ድጋፍ እንደሚያደርግና ልምዱን እንደሚያካፍል ጠቁመው፤ ይህ ስልጠና ባለሙያዎች ተጨማሪ እውቀትና ክህሎት አግኝተው ለማሕበረሰቡ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት እንዲሰጡ በማለም የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማሕበረሰብና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ተደራሽ ፕሮጀክቶች በመስራት፣ አጫጭር ስልጠናዎች በመስጠት፣ ህግ የማማከር አገልግሎት በመስጠትና ሙያዊ በጎ ፍቃድ አገልግሎት በመስጠት ለአካባቢው ማሕበረሰብ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አስታውሰው፤ ይህ ስልጠና ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎችና መሰረታዊ የቤተ ሙከራ ጥራት አተገባበር ዙሪያ ከተመረጡ ሆስፒታሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች በዘርፉ በቂ እውቀትና ልምድ ባላቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እንዲሰጥ መደረጉን ገልጸዋል።
አቶ ተካልኝ አክለውም፤ ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀትና ልምድ ወደ ተግባር የሚቀይሩበትና ከዩኒቨርስቲው ጋር በጋራ የሚሰሩበት እንዲሁም ቁጥጥርና ክትትል የሚደረግበትን የጋራ ስርዓት መዘጋጀቱን አስገንዝበዋል።
ከአሰልጣኞች መካከል አቶ አስቻለው ገመዳ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የጤና እና ሕክምና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል የቤተሙከራ ጥራት ቁጥጥር አስተባባሪ፤ ስልጠናው ባለሙያዎች ከዚህ በፊት በንደፈ ሀሳብና በተግባር የሚያውቋቸውና ሲተገብሯቸው የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት፣ የእርስ በርስ ልምድ በመለዋወጥ፣ በዩኒቨርስቲው ቤተሙከራ የተግባር ስራ በማስራትና የአሰራር ስርዓቱን በማሳየት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠታቸውን ነግረውናል።
ወ/ሮ ለምለም ከበደ ከሰልጣኝ የሕክምና ቤተሙከራ ባለሙያዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ በስልጠናው ከመረጃ አያያዝ ጀምሮ የቤተሙከራ ጥራት፣ የውጤት አያያዝ፣ የተካሚ አያያዝና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በቂ እውቀትና ልምድ ያገኙበት ስልጠና እንደነበር ገልጸውልናል።
ከሰልጣኝ የጤና ባለሙያዎች መካከል ዶክተር ዮናታን የኔሰው፣ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ዙሪያ በተለይም የደም ግፊት፣ የሰኳር ሕመም፣ የኩላሊት ሕመምና እና ሌሎች የጤና እክሎች በዩኒቨርሲቲው ባለሙያዎች የተሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ለታካሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት የራሱ እገዛ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲዲላ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et