ዲ.ዩ፤ ታህሳስ 12/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ.)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ት/ቤት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) ጋር በመተባበር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ነጻ የሕግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎች እና በሕግ ት/ቤት ለሚማሩ የሕግ ተማሪዎች በመሬት ሕግ፣ በውርስ ሕግ፣ በቤተሰብ ሕግና በፍትሐ ብሔር ስነ-ስርዓት ሕግ ላይ ለሦስት ቀናት የቆየ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
አቶ ኃይለማርያም ማሞ፣ የዲላ ዩኒቨርሰቲ ሕግ ት/ቤት ዲን፤ ስልጠናው በዋናነት በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማን ጨምሮ በሚገኙ ሰባት የዩኒቨርሲቲው ነጻ የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ላይ ለሚሰሩ የሕግ ባለሙያዎች እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሕግ ት/ቤት የሚማሩ ተማሪዎች በማዕከላቱ ላይ ነፃ የሕግ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ወደ ማዕከላቱ የሚመጡ የተለያዩ ጉዳዮችንና ባለጉዳዮችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው መሠረታዊ የሆኑ የሕግ ዕውቀቶችን ማስጨበጥ አላማ ያደረገ ስልጠና መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኃይለማርያም አክለውም፤ የህግ ትምህርት ክፍል ተማሪዎች ከ3ኛ ዓመት ጀምሮ በፅንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን ትምህርት በተግባር ልምምድ ለማድረግ በነፃ የሕግ ማዕከላት ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ ከውርስ ሕግ፣ ከቤተሰብ ሕግ እና ከመሬት ሕግ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ግጭቶች ብዙ ጊዜ ወደ ሕግ አገልግሎት ማዕከላት የሚመጡ ጉዳዮች መሆናቸውን በጥናት የተለዩ መሆኑን አቶ ኃይለማርያም አንስተዋል።
አቶ ንዋይ መንግስቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የስደተኞች ኮሚሽን (UNHCR) የዲላ ማዕከል ሲኒየር ፕሮቴክሽን አሶሼት በበኩላቸው፤ ለሰልጣኞቹ የፆታዊ ጥቃትና ብዝበዛ ጥበቃ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ ጥቃት እና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
ሌላው አሰልጣኝ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕግ የሕግ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አዲስ ታምሩ፤ ስልጠናው በዋናነት ሰልጣኞች በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ የተማሩትን ወደ መሬት አውርደው እንዴት መተግበር እንዳለባቸው የሚያሳይ ስልጠና እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ ነፃ የሕግ አገልግሎት ዲላ ማዕከል የሕግ ባለሙያ ወ/ሪት እህትአገኘው ንጉሴ እንዲሁም የሕግ ት/ቤት 5ኛ ዓመት ተማሪ ግሩም ፈለቀ፤ ስልጠናው በትምህርት የሚታወሱትን ብቻ ሳይሆን በፍርድ ቤት ያለው እያንዳንዱ የሕግ ጉዳይ እንዴት መታየት እንዳለበት ቁጭ ብለን በጥልቀት በመወያየት የሕግ ዕውቀታቸንን እንድናሰፋ እንድናስተካክል እገዛ የፈጠረ ስልጠና ነበር ሲሉ ገልጸዋል::
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
Telegram: https://t.me/dprd9
Email: pirdir@du.edu.et
p.o.box: 419
Dilla, Ethiopia