ዲ.ዩ፤ ሰኔ 25/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከጌዴኦ ዞን አስተዳደር ጋር በትብብር የሚያሰሩት የመረጃ ስርዓት ልማት ፕሮጀክት የአጋማሽ ዘመን ግምገማ ዎርክሾፕ (MID TERM REVIEW WORKSHOP ON DEVELOPING GEO DATA BASE FOR COMPREHENSIVE INVENTORY OF RESOURCES OF GEDEO ZONE) ተካሂዷል ።
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በመርሐ ግብሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ በስርዓት ተደራጅቶ የተቀመጠ መረጃ ለመንግሥት፣ ለፓሊሲ አውጪዎች፣ ለባለሀብቶች፣ ግብረሰናይ ድርጅቶችና ለማንኛውም አካል የሚፈልገውን ስራ ለመስራት ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቁመው፤ ፕሮጀክቱ የዞኑን ሁሉን አቀፍ መረጃ ሰብስቦ በዲጂታል መልክ በአንድ ማዕከል አደራጅቶ ለማስቀመጥ እስካሁን የሰራው ስራ አበራታች በመሆኑ ቀሪ ስራው በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቅ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ተናግሯል።
አብዮት ለገሰ (ዶ/ር)፣ የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ በበኩላቸው፤ ፕሮጀክቱ በዲላ ዩኒቨርሲቲና ጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ በትብብር ከ13 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቦለት በአራት ዓመት ውስጥ የጌዴኦ ዞን ሁሉም አቀፍ መረጃ ሰብስቦ በዲጂታል ስርዓት በአንድ ቋት በዞኑ ማዕከል ለማስቀመጥ ባለፉት ሁለት ዓመት ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ባሉት ቀበሌዎች የሚመለከታቸውን ባለሙያዎች በማሰልጠን ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመጠቀም ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ አስፈላጊ የሚባሉ መረጃዎችን መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
ዶ/ር አብዮት፣ አክለው የዛሬውን መድረክ ባለፈው ከተካሄዱት የማስጀመሪያ መርሐ ግብርና የፕሮግረስ ግምገማ ቀጥሎ ሶስተኛውና የአጋማሽ ዘመን የተከናወነው ስራ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በማቅረብ የደረሰውን ደረጃ ለማሳየት እንዲሁም ያለውን ክፍተት ገምግሞ ተጨማሪ ግብአቶችን በማካተት ወደ ቀጣይ የስራ ምዕራፍ ለመሸጋገር ያለመ የግምገማ ዎርክሾፕ መሆኑን አስረድተዋል።
መምህር አስፋው ማስረሻ የጥናት ቡድኑ አባል በፕሮጀክቱ የተሰራውን ስራ፣ ያጋጠመው ተግዳሮቶችና በቀጣይ የስራ እቅድ ለመድረኩ መነሻ ጽሑፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል።
ታጠቅ ዶሪ (ዶ/ር)፣ የጌዴኦ ዞን የግብርና መምሪያ ኃላፊና የጌዴኦ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር፤ ፕሮጀክቱ መረጃዎችን በሳይንሳዊና በዘመናዊ መልኩ ሰንዶ በማስቀመጥ ለሁሉም ስራዎች መነሻና ማሳለጫ ሁኖ እንደሚያገለግል አመላክተው፤ ለተመራማሪዎች እንዲሁም ለዲላ ዩኒቨርሲቲ ምስጋና አቅርበዋል።
በዎርክሾፑ ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አመራሮች እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et