ዲ.ዩ፤ ግንቦት 14/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ከጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ጋር በመሆን የቀረጸውንና ለ4 ዓመት ይቆያል የተባለውን የማህበረሰብ አቀፍ አጋርነት ፕሮጀክት ትልም ግምገማ) (Community Engagemeng Project Proposal Defense) አካሂዷል።
በመድረኩ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት የሆኑት ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የገጠመንን የትምህርት ስብራት ለማከም ዩኒቨርሲቲያችን የድርሻውን ለመወጣት ጥናት አካሂዶ በጌዴኦ ዞን ከሚገኙ ት/ቤቶች መካከል 5ቱን በመለየት በቀጣይ አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ፕሮጀክት መንደፉን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለው፤ ጥናት የተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች ላለፋት ሶስት አመታት ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ መላክ ያልቻሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዛሬ ለግምገማ የቀረበው የፕሮጄክት ትልም ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ታቅዶ የተዘጋጀ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር፣ አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ በዩኒቨርሲቲው የሚገኙ ሶስት ኮሌጆች ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ጋር በመሆን በሰሩት ጥናት መነሻነት የተቀረጸ ፕሮጄክት መሆኑን ገልጸው፤ ጥናቱ ለምሁራን ቀርቦ መገምገሙንና ሃሳብ አስተያየቶች የተሰጡበት መሆኑን ገልጸዋል።
የፕሮጄክቱን ትልም ያቀረቡት ተመስገን ንጉስ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ፤ ፕሮጄክቱ ረጅም ጊዜ ተወስዶ የተቀረጸ መሆኑን ገልጸው፤ በመድረኩ የተሰጡ ሐሳብ አስተያየቶች በግብዓትነት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል። ፕሮጄክቱ ከ9-12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን ያማከለ እንደሆነም ዶ/ር ተመስገን አስረድተዋል።
አቶ ንጹህ ከበደ፣ የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ የመምህራን ልማት ዳይሬክተር፤ በተደረገው ጥናት ለትምህርት መውድቅ ዋናው ምክንያት የተማሪዎች ፍላጎት ማጣትና የመምህራን ክህሎት ማነስ መሆኑን አንስተው፤ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ተባብሮ በመስራት የተጠቀሱትን ክፍተቶች ለማረም ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et