ዲ.ዩ፤ መጋቢት 25/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የሴቶችን የአመራርነትና የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጎልበት ለዲላ ከተማ ምክር ቤት ሴት ተመራጮችና አመራሮች የአቅም ግንባታ ሰልጠና ተሰጥቷል።
ስልጠናውን የዲላ ከተማ ምክር ቤት፣ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት እንዲሁም ከ UIID ፕሮጀክት ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የዲላ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የተከበሩ ወ/ሮ ሊዲያ ከበደ እንደገለጹት፤ አሁን ላይ እንደ ሀገር በሴቶች ላይ ለውጥን ካላመጣን በሀገር ደረጃ ይመጣል ብለን የምናስበውን ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ ስለማይቻል በዚህ ላይ እንደ ዲላ ከተማ ሰፊ ስራዎች በመስራት በከተማው በየደረጃው ላሉ ሴት አመራሮች የሴቶችን የመሪነትና የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጎልበት የሚሰጥ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል።
ክብርት ወ/ሮ ሊዲያ አክለውም፤ ይህ ስልጠና አሁን ላይ በከተማው በአመራርነት ደረጃ ወደ 22 በመቶ ያለውን የሴቶች ተሳትፎ በሂደት ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።
አቶ ፈጠነ ባሌሲ፣ በማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ስልጠናና ማማከር ኦፊሰር፤ ስልጠናው የዲላ ከተማ ምክር ቤት በከተማው ላሉ ሴት አመራሮች የመሪነት ሚናን ለማሳደግ በጋራ ለማዘጋጀት በጠየቀው መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ UIID ፕሮጀክት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር እና ከምርምር ስራዎች ባለፈ እንዲህ ያሉ የትብብር ስራዎችን በአቅራቢያው ከሚገኙ ከሁሉም የማህበረሰብ አካላት ጋር በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ፈጠነ አያይዘው ተናግረዋል።
ከአሰልጣኞች መካከል በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ዕቅድ እና ሥራ አመራር ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ብርሃኑ ሞያታ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ስልጠናው የሴቶችን የአመራርነት ሚና ለማሳደግ የተዘጋጀ እንደመሆኑ የሴት አመራሮችን የአመራርነት እና የውሳኔ ሰጪነት ሚናን ለማጎልበት ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንደሆነ ተናግረዋል።
በስልጠናው መዝጊያ ላይ ንግግር ያደረጉት የተከበሩ ወ/ሮ ፈትለወርቅ በቀለ፤ የዲላ ከተማ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ፤ የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በምክር ቤት ደረጃ እንደዚህ አይነት ስልጠናዎች ሲሰጡ የመጀመሪያ እንደሆነ ገልጸው፤ ሰልጣኞች ከስልጠና በኃላ ወደ ምክር ቤቱም ይሁን ወደየ ሴክተሩ ሲመለሱ ባሉበት የአመራርነት ቦታ ላይ የተሻሉ ለውጦችን በማምጣት የመረጣቸውን ህዝብ ጥያቄ መመለስ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በዚህ ረገድ ምክር ቤቱ ላቀረበው ጥያቄ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለሴት አመራሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ስልጠና በመስጠቱ ክብርት አፈ ጉባኤዋ በምክር ቤቱ ስም ለዩኒቨርሲቲው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ስልጠናውን ሲሳተፉ ያገኘናቸው ከዲላ ከተማ ምክር ቤት የመጡት ሰልጣኝ ክብርት ወ/ሮ ነፃነት አለሙ፣ እንዲሁም ከሀሮ ሬሳ ቀበሌ የመጡት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ተረፈች ወራሳ እንደገለጹት፤ ስልጠናው ከዚህ ቀደም ህዝብን መሰረት አድርገው እየሰሯቸው በነበሩ ስራዎች ውስጥ እንደ ሴት አመራር ሚናቸውን የተወጡበት እና ያልተወጡበት ሁኔት ምን ነበር ሰፊ ትምህርት ያገኙበት እና በስራዎቻቸው ውስጥ ያጋጠሙ ጉድለቶችን እንዲያርሙ ግንዛቤ የፈጠረላቸው ስልጠና እንደነበር ገልጸውልናል።
በቀጣይም በከተማው ውስጥ በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ሴት አመራሮች በቁጥር ብዙ እንደመሆናቸው እንዲህ ያሉ ስልጠናዎች ብዙዎችን አሳታፊ ባደረገ መልኩ ቢሰጡ ሴት አመራሮች ላይ ትልቅ እምርታ ማምጣት እንደሚቻል ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።
በስልጠናው የዲላ ከተማ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች እና የቀበሌ አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ ከ50 በላይ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ሴት አመራሮች ተሳትፈዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
ለወቅታዊ መረጃዎች
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: pirdir@du.edu.et