ዲ.ዩ፤ ነሐሴ 18/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት ከኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር የተዘጋጀው “የግብርና ቆጠራ ለመረጃ ምሉዕነት” በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ግብርና ናሙና ቆጠራ ባለሙያዎች ስልጠና የማስጀመሪያ መርሐ ግብር በዲላ ዩኒቨርሲቲ በዛሬው ዕለት ተከናውኗል።
ደረጃ ክፍሌ (ዶ/ር)፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሐሴዴላ ግቢ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፤ ዩኒቨርስቲው ለሰልጣኞች የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት የመኝታ፣ የምግብ፣ የሕክምና፣ የመዝናኛ፣ የደህንነት ጥበቃ፣ ስልጠና የሚሰጥባቸው ክፍሎች እና የሚያስልጉ አቅርቦቶች ዝግጅት መጠናቀቁን በመግለፅ የተቋሙን ህግና ደንብ በማክበር አገልግሎቶችን በማግኘት መልካም ቆይታ እንዲኖራቸው ተመኝተዋል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንትና የፕሬዚዳንቱ ተወካይ በመርሐግብሩ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፤ ግብርና የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት መሆኑን በማንሳት ሰልጣኞች የተሰጣቸው ሀላፊነት ትልቅ መሆኑን አውቀው ስልጠናው በንቃት መከታተልና ለስራ በሚሰማሩበት አካባቢ የሚሰበስቡት መረጃ ለአገር ቀጣይ እድገትና ብልፅግና ወሳኝ ሚና እንዳለው ተረድተው ሀላፊነታቸውን በጥንቃቄ እንዲወጡ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ማቲዎስ ሀብቴ (ዶ/ር)፣ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ተወካይ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለአገር እድገትና ልማት አስተዋፅኦ የሚያበርክት የተማረና የሰለጠነ ዜጋ በማፍራት አበረታች ስራዎች እያከናወነ ያለ ተቋም መሆኑን በመጥቀስ፤ መንግሥት የሚቀርፃቸውን ፖሊሲዎችና የልማት ስራዎች በመደገፍ የተለያዩ ስልጠናዎችን መስጠቱን በማስቀጠል ከኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎትና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የግብርና ናሙና ቆጠራ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ዶ/ር ማቲዎስ አያይዘውም፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ ተልዕኮ ልየታ የተግባር ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ ግብርናን ከአራቱ የትኩረት መስኮቹ አንዱ አድርጎ እየሰራ ያለ በመሆኑ ሰልጣኞች ለስራቸው የሚያስፈልጋቸውን በቂ እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ የካበተ ልምድ እንዳለው አስገንዝበዋል።
አቶ ናቃቸው ነጋሽ፣ በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በሀዋሳ፣ ዲላ እና መደወላቡ ክላስተር ማዕከላት አስተባባሪ፤ ከ2016 -2018 ዓ/ም የሚተገበረው የመካከለኛ ዘመን የስታቲስቲክስ ፕሮግራም አካል የሆነውና መንግሥት፣ የምርምር ተቋማት፣ የቢዝነስ ድርጅቶችና ህዝብ የሚጠቀምበትን የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ የሚያስፈልገውን መረጃ ለመሰብሰብ የሚችል ብቁ እና ትጉህ ሰልጣኝ በማስመረቅ ወደ ስራ ለማሰማራት ታቅዶ የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ጠቁመው፤ በአገር ደረጃ በ45 ዩኒቨርሲቲዎች ለተካታታይ 25 ቀናት በግብርና ናሙና ቆጠራ ዙሪያ እዲሚሰጥና በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከጌዴኦ ዞን፣ ከኮሬ ዞን እና ከቡርጂ ዞን የተወጣጡ 609 ባለሙያዎች ስልጠና እንደሚከታተሉ ገልጸዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et