ዲ.ዩ፤ ሰኔ 20/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የ2016 ዓ/ም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ወሰን ተሻጋሪ ልዩ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ በዛሬው እለት ተጀምሯል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር፤ ወጣቶች በራሳቸው ተነሳሽነት፣ መልካም ፍቃድና ፍላጎት ተንቀሳቅሰው የማሕበረሰብ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያበረክቱት አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው፤ በጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመስጠት ከተለያዩ የሀገራችን ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ወጣቶች በጎ አገልግሎት ስራቸውን እውን እንዲሆን ዲላ ዩኒቨርሲቲ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ አስገንዝበዋል።
አቶ በቀለ ሎኮርማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሠላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ በበኩላቸው፤ በጎ ፍቃድ አገልግሎት እድሜና ፆታ፣ ማሕበራዊ ደረጃ፣ መልከዓ ምድራዊ ወሰን ሳይገድበው የሰብአዊነት መርህ ላይ ብቻ መሰረት በማድረግ የሚከናወን ተግባር መሆኑን አንስተው፣ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የመጡ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ክልሉ ሰላማዊ ሕብረተሰቡን እንግዳ ተቀባይ መሆኑን ተረድተው በጎ ስራቸውን በአግባቡና በተረጋጋ ሁኔታ እንዲያከናውኑ የክልሉ መንግሥት ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ዳንኤል ሽፈራው፣ የዲላ ከተማ ከንቲባ፤ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተግባራት መሳተፋቸው የማሕበረሰቡን መልካም እሴቶች እንዲቀስሙ፣ ለማሕበረሰባቸው የተቆርቋሪ እና ሀየኃላፊነት ስሜት እንዲያዳብሩ፣ ከአልባሌ ቦታዎች ርቀው ለማሕበረሰቡ ጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲሁም የሀገራቸውን ታሪክና መልክዓ ምድር እንዲያውቁ እድል እንደሚፈጥርላቸው አመላክተው፣ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ቆይታቸው የዲላ ከተማ አስተዳደር በቅርበት እንደሚያግዛቸው አስገንዝበዋል።
ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከ700 በላይ ወሰን ተሻጋሪ የክረምት በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች በዲላ ከተማና አከባቢው ለሚኖር ማሕበረሰብ በክረምት ወቅት የተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et