ዲ.ዩ፤ ግንቦት 12/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ዜሮ ፕላን ፕሮግራም (0 – Plan) ዓመታዊ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ዝግጅቶች አክብሯል።
አቶ ቢኒያም ሺፈራው፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ ዜሮ ፕላን በ2005 ዓ/ም ሲሰጥ በነበረው የህይወት ክህሎት ስልጠና እንደ ሀሳብ ተነስቶ ወደ ፕሮግራም ለማሳደግ የዩኒቨርስቲውን ማኔጅመንት ፍቃድ አግኝቶና አጋር ድርጅቶችን በማፈላለግ በሴቶች የስነ ተዋልዶ ጤና ትኩረት በመስጠት መጀመሩን አስታውሰው፤ በዚህ ሰዓት በሁሉም የዩኒቨርስቲው ግቢዎች በሴቶችና በወንዶች የመኖሪያ ህንፃዎችን ምቹና ማራኪ ክፍሎች በማዘጋጀት የተማሪዎች የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮችና በተለያዩ ምክንያት የትምህርት ውጤት ማሽቆልቆልን ወደ ዜሮ ለማውረድ ወይም ችግሩን ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ የሚሰራ ፕሮግራም መሆኑን አስረድተዋል።
አቶ ቢኒያም አክለው፤ የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች በበጎ ፍቃዳቸው አባል የሚሆኑ ተማሪዎች አስተባባሪዎቻቸውን በየዓመቱ እየመረጡና እየተኩ በአገር ደረጃ አበረታችና አርአያ የሆኑ ስራዎች በመሰራታቸው ትምህርት ሚኒስቴር የ ዜሮ ፕላን ፕሮግራም ተሞክሮዎችን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በመውሰድ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለማስፋፋት በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከተመሰረተበት የመጀመሪያ ዓመት ጀምሮ የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ክንውኖች እንደሚያከብርና ተመርቀው የወጡ ተማሪዎች በበዓሉ ላይ በመገኘት የህይወት ተሞክሮዎቻቸውንና ልምዳቸውን እንደሚያካፍሉ አንስተው በዘንድሮው ዓመታዊ በዓልም ከአዲስ አበባና ከተለያዩ አካባቢዎች በመምጣት ልምድና ተሞክሮዎችን በማካፈል እንዲሁም ለዜሮ ፕላን ክፍሎች ማስዋቢያ እቃዎችና አንሶላዎች ይዘው በመምጣት በቀድሞ ቤታቸው ተገኝተው ከእህት ወንድሞቻቸው ጋር በመሆን የምስረታ በዓሉን በደማቅ ሁኔታ እንዲከበር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን አቶ ቢኒያም ገልጸዋል።
እሌኒ ግርማ፣ በኦዳያአ ግቢ የሴት ተማሪዎች ዜሮ ፕላን ፕሬዝዳንት፤ በፕሮግራሙ የቤተ -መጻህፍት አገልግሎት፣ የአቻ ለአቻ ውይይት የሚካሄድበት፣ የህይወት ክህሎት ስልጠና የሚሰጥበት፣ የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙበት፣ ችግር ለገጠማቸው ተማሪዎች የማገገሚያ ክፍል፣ የጥሞና ክፍል፣ የልዩ ልዩ ተሰጥኦ ማበልፀግያ ክፍል፣ የመዝናኛና ሌሎች ክፍሎች ፕሮግራሙን በፍቃዳቸው ለሚቀላቀሉ ተማሪዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጻለች። አያይዛም፤ ዜሮ ፕላን ተማሪዎች እንደ ቤተሰብ ለደስታም ሆነ ችግር በጋራ የተሻለ ውጤት አስመዝግበው ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው ብሎም ለአገር ጠቃሚ ዜጋ ሆነው እንዲወጡ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ፕሮግራም መሆኑን በመግለጽ፤ ሌሎች የዩኒቨርስቲው ተማሪዎችም አባል በመሆን በዚህ ፕሮግራም ተጠቃሚ እንዲሆኑ መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ሳምራዊት አበራ፣ የ2010 ዓ/ም ተመራቂ፤ ዜሮ ፕላን ትምህርቷን በአግባቡ እንድትከታተል፣ በራሷ እንድትተማመን፣ ከሰው መግባባት እንድትችልና መሪነትን እንድትማር በማድረግ አሁን ላለችበት ህይወት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላት ገልጻ፤ ይህን ውለታ በማሰብ ፕሮግራሙን ያሳየውን ለውጥ ለመመልከት፣ ከጓደኞቿ ጋር ለመገናኘትና ልምዷን ለተማሪዎች ለማካፈል መምጣቷን እንዲሁም ባየችው ለውጥም ደስተኛ መሆኗን ገልፃለች።
ሮብሰን ጣለው፣ የ2014 ዓ/ም ተመራቂ ዜሮ ፕላን የትምህርቱን ውጤት ከማሻሻልና የስነ ተዋልዶ ጤና ከማወቅ ባሻገር ተመርቀው ከወጡ በኋላ የቤተሰብ ግንኙነት በማስቀጠል በአዲስ አበባ የሚገኙት በየወሩ እንደሚገናኙና በተለያዩ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም በመሰብሰብ በደስታም በችግር እንደሚጠያየቁና እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ ጠቅሶ፤ በተቋሙ የተጀመረውን የቤተሰብ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠልና የዜሮ ፕላንን የቀጣይ እድገት የድርሻውን ለመወጣት በምስረታ በዓሉ መገኘታቸውን ገልጿል።
በምስረታ በዓሉ አከባበር የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ዳይሬክቶሬት ሀላፊዎችና ሰራተኞች፣ የቀድሞ ተማሪዎች፣ የአሁኑ ተማሪዎችና አስተባባሪዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በመታደም የዜሮ ፕላን ክፍሎች በመጎብኘት፣ የህይወት ተሞክሮና ልምድ በመቀያየር፣ የቀጣይ ስራ እቅድ በመወያየትና የመዝናኛ ፕሮግራሞች በመከወን የምስረታ ቀን በዓሉ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et