ዲ.ዩ፤ መጋቢት 05/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ 2ተኛውን ሳምንት የላብራቶሪ ኤግዚብሽን አካሂዷል።
አቶ ዮናስ ተጠምቀ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ ላብራቶሪዎች ከፍተኛ በጀት ወጥቶባቸው የተገነቡ እንደመሆናቸው መጠን አጠቃላይ የኮሌጁ መምህራንና የላብራቶሪ አሲስታንቶች ላብራቶሪዎችን በሚገባ ተጠቅመው ከመማር ማስተማሩ ባለፈ ለተቋሙ የገቢ ምንጭነትም ጭምር እንዲሆኑ ማስቻል እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።
አንተነህ ወጋሶ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ ዲን በበኩላቸው፤ የኢግዚብሽኑ ዋና ዓላማ በኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ኮሌጅ የሚገኙ ላብራቶሪዎችን እንዴት አድርገን በተገቢው ሁኔታ በመጠቀም ማስተማር እንችላለን የሚለውን ለመለየት እና ላብራቶሪዎች ፋብሪካው ከሰጠው ኦፕሬሽናል ማንውል ውጪ ኮርስን መሰረት ያደረገ የላብራቶሪ ማንዋል መዘጋጀት ስላለበት ይሄን ለማስጀመር ታሳቢ ያደረገ ፕሮግራም ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል።
ኤግዚብሽኑ ባለፈው ሳምንት በመካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍል ሲጀመር የተገኙ ግብአቶች እጅግ ጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ አብዛኛው ላብራቶሪዎች የተሻሉ ከመሆናቸው አንጻር ከመማር ማስተማር ባለፈ ለምርምርም ጭምር የሚሆኑ፣ አንዳንዶቹም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር የማይገኙ በመሆናቸው እነዚህን ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችና የመንግስት ተቋማትም ጭምር የማሳወቁን ስራ ለመስራት ከዩኒቨርሲቲው የበላይ አካላት ጋር ንግግር መጀመሩን ዶ/ር አንተነህ አያይዘው ገልጸዋል።
እንደ ዶ/ር አንተነህ ገለፃ ፤ እነዚህ ላብራቶሪዎች ለተለያዩ ስራዎች የሚያገለግሉ እንደመሆናቸው ከመማር ማስተማር ባለፈ ለተቋሙ ገንዘብ ማመንጫም ጭምር እንዲሆኑ ለማስቻል አሁን ላይ ስራዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።
መ/ር ኤልያስ ማሙሸት፣ የኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና ትምህርት ቤት ዲን በበኩላቸው፤ በኮሌጁ በተያዘው ማንዋል መሰረት እንደሌሎቹ የትምህርት ክፍሎች በኤሌክትሪካልና ኮምፒውተር ምህንድስና ት/ቤት ስር የሚገኙ ላብራቶሪዎች በኤግዚብሽኑ እንደቀረቡ ገልጸው፤ እነዚህ በትምህርት ክፍሉ ያሉ ላብራቶሪዎች ከዚህ በፊት በካምፓኒው ከተዘጋጀላቸው ውጪ ማንዋል ያልነበራቸው በመሆኑ ይህ ኤግዚብሽን እነዚህን ማንዋሎች ለማስጀመር ጭምር የተዘጋጀ ፕሮግራም እንደሆነ ገልጸውልናል።
ይህ የላብራቶሪ ኤግዚብሽን ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት 4 ሳምንታት ሲቀጥል ከኮሌጁ የሀይድሮሊክስ፣ የሲቪል፣ የምግብ፣ የኪነ ህንፃ ምህንድስና እና የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍሎች ኤግዚብሽኑ ላይ ላብራቶሪዎቻቸውን የሚያቀርቡ መሆናቸው ከኮሌጁ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲዲላ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et