ዲ.ዩ፤ ሚያዝያ 11/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በአቶ ተካልኝ ገሎ የተመራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልኡካን ቡድን የዲላ ዩኒቨርሲቲ “STEM” ማዕከልን ጎብኝቷል።
ችሮታው አየለ (ደ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለልኡካን ቡድን አባላት የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ጋር በአገር ልማትና እድገት ዙሪያ በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፤ በተለይም በዲጂታል ኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በአይሲቲ ልማት፣ በችግር ፈቺ ፈጠራዎችና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት ለመስራት ተቋማችን ዝግጁ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ ተካልኝ ገሎ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ “STEM” ማዕከል በማደራጀት የፈጠራ ዝንባሌ ያላቸውን ተማሪዎች በመቀበል ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራ ማመንጨት እንዲችሉ የንድፈ ሀሳብና የተግባር ትምህርት በመስጠት ተማሪዎች አመርቂ ስራዎችን እንዲሰሩ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በመሆኑ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ተካልኝ አያይዘውም፤ በጉብኝታቸው ወቅት የተመለከቷቸው የፈጠራ ውጤቶች ወደ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ተቀይረው ለባለፈጠራዎቹ የድካማቸውን ዋጋ የሚያገኙበት እንዲሁም ለአካባቢው ማሕበረሰብ ችግሩን የሚፈታበት እንዲሆን ቢሯቸው ከዲላ ዩኒቨርሲቲና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
ሀብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት፣ በጉብኝቱ መርሀ ግብር ባሰሙት ንግግር፤ “STEM” ማዕከል የሚማሩ ተማሪዎች በየዓመቱ እንደሚመረቁና የራሳቸውን ችግር ፈቺ ፈጠራ ሥራ ሰርተው በሚዘጋጀው አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ጥሩ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሚገኙና ይህ ውጤት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብሎም ፍሬ እንዲያፈራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር በአጋርነት እንዲሰራ ጠይቀዋል።
አቶ ተስፋጽዮን ዳካ፣ የጌዴኦ ዞን መንግሥት ረዳት ተጠሪ፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂና ፈጠራ እውቀት ለማስፋት “STEM” ማዕከል በማደራጀት በጌዴኦ ዞንና አጎራባች ክልል ወረዳዎች ተማሪዎችን በማስተማር አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ላይ እንደሚገኝ አመላክተው፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ ኃላፊና ማኔጅመንት አባላት ያደረጉት ጉብኝት አስፈላጊና ወቅታዊ መሆኑን ተናግረዋል። ማዕከሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጌዴኦ ዞን አስተዳደር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ተስፋጽዮን አያይዘው ገልጸዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በማዕከሉ ከተሰሩ ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎች ለጎብኝዎች ቀርበው ገለጻ ተደርጎባቸዋል።
በጉብኝት መርሃ ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቢሮ የበላይ አመራሮች፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር አመራሮች፣ የጌዴኦ ዞን የሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ አመራሮች፣ የማዕከሉ መምህራን፣ ተማሪዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et