ዲ.ዩ፤ ሰኔ 27/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ መረሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 2,356 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ለ 2016 ዓ/ም ተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች፣ እንዲሁም ተማሪዎችን ለምረቃ መብቃት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው፤ ተመራቂዎች ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰጠውን የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና አልፈው ለዛሬ የምረቃ ቀን መድረሳቸውን ገልጸው በተሰጠው የመውጫ ፈተና እንደ ዩኒቨርሲቲ 75.9 በመቶ ጥሩ ውጤት መመዝገቡንና በቀጣይ ከዚህ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።
መንግሥት በያዘው አጠቃላይ የትምህርት ሪፎርም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተልዕኮ የልየታና በትኩረት መስክ መሰረት ዲላ ዩኒቨርሲቲ የተግባር ዩኒቨርሲቲ (Applied Science University) በመሆን የተሰጠውን ተልዕኮ ለማሳካት ከበላይ አመራር ጀምሮ እስከ መምህራንና ባለድርሻ አካላት በቂ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በመስጠት ወደ ትግበራ መግባት መጀመሩን ገልጸዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በቡና ሳይንስና ኢኮኖሚክስ በሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎች ማስመረቁን ዶ/ር ችሮታው አያይዘው ገልጸዋል።
የእለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትርና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ስብሳቢ ለተመራቂዎች በሰጡት የስራ መመሪያ፤ ምርቃት ተመራቂዎች ብሩህ ተስፋ የሚያዩበትና ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚሸጋገሩበት ድልድይ መሆኑን ጠቁመው፤ ትምህርት የሁሉም ልማቶች መሠረትና የሁሉም ችግሮች መፍቻ መሳሪያ በመሆኑ መንግሥት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ዩኒቨርሲቲዎች በጅምላ ሳይሆን በተልዕኮ ልየታና የትኩረት አቅጣጫ በመመደብ የልህቀት ማዕከል እንዲሁም በተሰጣቸው ተልዕኮ የላቀ አፈጻጸም እንዲያስመዘግቡ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ የዕለቱ ተመራቂዎች በብዙ ልፋትና ውጣ ውረድ የተሰጣችሁን የቤት ስራ በአግባቡ ተወጥታችሁ ለዚህ ስለበቃችሁ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት ተመራቂዎች በሚሄዱበት አከባቢ ሁሉ ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
አስናቀ ይማም (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራርና አልሙናይ ዳይሬክተር በዕለቱ በቅደመ ምረቃ 1899 ተማሪዎች፣ በሁለተኛ ዲግሪ 127፣ በድህረ ምረቃ ዲፕሎማ (PGDT) 226 ተማሪዎች፣ ከፍተኛ ዲፕሎማ 104፣ በአጠቃላይ 2,356 ተማሪዎች ለምረቃ መብቃታቸውን አብስረዋል።
በዕለቱ ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከማኔጅመንት ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው ተማሪ ሊቁ ንጉሴ አጠቃላይ ውጤት 4.00 በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
የማዕረግ ተመራቂ የሆነው ሊቁ ንጉሴ፣ በዩኒቨርሲቲው በነበረው የትምህርት ቆይታ በእንዲህ ባለ አስደሳች ውጤት ማጠናቀቅ መቻሉን የመምህራንና የወላጆች ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረበት ገልጿል።
በበዓሉ ላይ የእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት ክብርት ጫልቱ ሳኒ፣ የኢፌዴሪ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢን ጨምሮ፣ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የደቡብ ኢትዮጵያ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ የጌዴኦ ዞን፣ የዲላ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሴኔት አባላት፣ በተለያየ እርከን የሚገኙ የዲላ ዩኒቨርስቲ አመራሮችና መምህራን፣ አባገዳዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል አባላት ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቀውታል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et