ዲ.ዩ፤ ሰኔ 15/2016 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስና አጠቃላይ ሆስፒታል ለቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ አባላት የሽኝትና የእውቅና ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
አቶ መሳይ ፍቅሩ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ፤ የጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል የነበሩትን ክፍተቶች በመለየት የተሻለ የመማር ማስተማር ሂደት እና የሕክምና አገልግሎት እንዲኖር፣ ለአገልግሎት ምቹ ያልነበሩና ያረጁ ህንፃዎች እንዲታደሱ እንዲሁም ሌሎች ተቋማዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ በተደረገው ጥረት የቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ጠቁመው፤ የስራ አመራር ቦርዱ አባላት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የምስጋና እና እውቅና መስጠቱን ገልጸዋል።
አቶ ትዝለኝ ተስፋዬ፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ የቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ ወደ ስራ በገባበት ወቅት ሆስፒታሉ ሰፊ ክፍተቶች ይታይበት በነበረው ጊዜ መሆኑን አስታውሰው፤ ከዩኒቨርሲቲው አመራር፣ ከባለሙያዎች፣ ከአካባቢው ማሕበረሰብና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ቀንና ለሊት በመስራት የተሻለ ተቋም እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።
አቶ ተስፋጽዮን ዳካ፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ሆስፒታል የቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ላይ የነበሩን ክፍተቶች በመለየት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመናበብ አበረታች የሚባሉ ስራዎች ማከናወናቸውን አመላክተው፤ የሆስፒታሉ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በነበሩበት ወቅት ያካበቷቸውን ልምድና ተሞክሮዎች ለአዲሱ ስራ አመራር ቦርድ ለማካፈልና ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል።
አቶ ዳንኤል ሽፈራው፣ የዲላ ከተማ ከንቲባና የአዲሱ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፤ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና እንዲሁም የሆስፒታሉን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ከዩኒቨርስቲው አመራርና ሰራተኞች፣ የቀድሞ የቦርድ አባላት፣ ከአካባቢው ማሕበረሰብና አስተዳደር ጋር በመቀናጀት እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
የቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ አባላት ለአዲሶቹ የሆስፒታሉ ስራ አመራር ቦርድ አባላት ልምዳቸውንና ተሞክሮዎቻቸውን በማካፈል ውይይት ተደርጎና እየታደሱ ያሉ ህንፃዎች ተጎብኝተው፤ ለቀድሞ ስራ አመራር ቦርድ አባላት የእውቅናና የምስክር ወረቀት በመስጠት አሸኛኘት ተደርጓል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ፤
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
Facebook:
https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram: https://www.t.me
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et