በዝግጅቱ ላይ የተገኙ እንግዶችንና ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልዕክት ያስተላለፉት የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ- ሰብዕ ኮሌጅ ዲን ተወካይ መምህር እንግዳወርቅ እንድሪያስ፤ ወደ አረንጓዴዋ ምድር ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልዕክት በማስተላለፍ ዝግጅቱ ደራሲያንና ሌሎች የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች ልምዳቸውን የሚያጋሩቀትና የተለያዩ የሥነ ጽሑፍ ስራዎች ለታዳሚያን የሚቀርቡበት እንደሆነ ገልጸዋል ። መ/ር እንግዳወርቅ አክለውም፤ የዝግጅቱ ዋና ዓላማ ደራሲያንን ለአንባቢያን ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ በማድረግ የንባብ ተነሳሽነትን መፍጠር እንደሆነ ተናግረዋል ።
እንደ መምህር እንግዳወርቅ ገለጻ፤ በእርግጥ ከዚህ ቀደም በኮሌጁ ሥር ያሉ ትምህርት ክፍሎችም ሆነ ኮሌጁ እየተባበሩ የተለያዩ ደራሲያንን ያመጡ እንደነበር አስታውሰው ይህ ግን ከዛኛው የሚለየው ሌላ ጊዜ ጨርሶ በማይታሰብ መልኩ በቁጥር በርካታ ደራሲያን ዲላ እና ይርጋጨፌን መሠረት አድርገው የመጡበት እንደመሆኑ ዝግጅቱ ለኮሌጁም ሆነ ለዩኒቨርሲቲው ከስንት አንዴ የሚገኝ ትልቅ ዕድል እንደሆነ ተናግረዋል።
በዝግጅቱ ደራሲ ዘነበ ወላ እና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት እንዲሁም የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፎክሎር መምህር ዶ/ር ሰለሞን ተሾመን ጨምሮ ሌሎች የሥነ ጽሁፍ ባለሙያዎችም የብዙ ዓመታት የሥነ ጽሑፍ ተሞክሯቸውን መነሻ አድርገው ለዝግጅቱ ታዳሚ የንባብ ልምዳቸውን አካፍለዋል።
በተመሳሳይ ተወዳጇ ገጣሚ፣ የባላገሩ አይዶል የመድረክ አጋፋሪ እና የሲራኖ ቲያትር መሪ ተዋናይ ሆና የተወነች ተዋናይት፣ ገጣሚ ረድኤት ተረፈ፤ በ2009 ዓ.ም ካሳተመችው “አንድ ኅሙስ” ከተሰኘው የግጥም መድብሏ ግጥሞቿን ለታዳሚያን ያቀረበች ሲሆን የዲላ ዩኒቨርሲቲ መቅረዝ የሥነ ጽሑፍ ክበብ አባላትም የግጥም ስራዎቻቸውን አቅርቀዋል።
በዝግጅቱ መጨረሻም በቅርቡ ህይወቱ ያለፈው የዲላ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ ትምህርት ክፍል አንጋፋ የሥነ-ጽሑፍ መምህር ቴዎድሮስ ቦጋለን ስብስብ ስራዎች የያዘና በትምህርት ክፍሉ መምህራን ጥረት “የሥነ-ጽሑፍ ፈርጀ ብዙ ሰበዞች” በሚል ርዕስ ለህትመት የበቃው መጽሐፍ በመድረኩ ለተገኙ ደራሲያንና የሥነጽሑፍ ባለሙያዎች ተበርክቷል።
በሥነ ጽሑፍ ዝግጅቱ የኢትዮጵያ ቤተ -መዛግብትና ቤተ-መጻሕፍት አገልግሎት ተወካዮችን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ አንጋፋ የኪነ ጥበብ ሰዎች ፣ መምህራን፣ ገጣሚያን፣ ደራሲያን፣ ተዋንያን እና የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪያን እንዲሁም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
ዲላ፤
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
FB: https://www.facebook.com/Du.edu.et
Telegram:https://t.me/dprd9
website: https://www.du.edu.et
Email: https://www.pirdir@du.edu.et