በቨርሚ ኮምፖስት የአፈር ማዳበርያ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ዙሪያ በወናጎ እና አባያ ወረዳ ለሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች ስልጠና ተሰጠ።

ዲ.ዩ. ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ.) የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ከግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ኮሌጅ ጋር በመተባበር በቨርሚ ኮምፖስት የአፈር ማዳበሪያ አዘገጃጀትና አጠቃቀም ዙሪያ ወናጎ እና አባያ ወረዳ ለሚገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች ስልጠና ሰጠ።
ሞዴል አርሶ አደሮች ከስልጠናው በኃላ በራሳቸው ማሳ ላይ ኮምፖስቱን ማምረት እንዲችሉ የተለያዩ የተግባር ስልጠናዎች መሰጠቱን የገለጹት የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቴር አቶ ክብሩ አለሙ ቴክኖሎጂው ቀለል ያለ በመሆኑ ሁሉም በአካባቢው ለማምረት የሚያስችል ሲሆን በአፈር ለምነት ምክንያት ተፈጥሮ የነበረውን የምርታማነት ችግር የመቀረፍ ዕድሉ ከፍ ያለ እንደሆነም ገልጸዋል።
አቶ ክብሩ አያይዘውም በፕሮጀክቱ ቀጣይ ስራ ላይ በወረዳዎቹ የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎች፣ የቀበሌ አመራሮች እና ባለሀብቶች በተገኙበት ሰፊ ውይይት ተካሂዶ በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ተግባራት ከባለ ድራሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል።
ስልጠናውን ከሰጡት መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሃብት ትምህርት ክፍል መምህርና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከበደ በበኩላቸው የስልጠናው ዋና ዓላማ በአካባቢያችን ተጥሎ አካባቢን እየበከለ ያለውን የቡና ገለፈት ወደ አፈር ማዳበሪያነት በመቀየር አርሶ አደሩ ጋር ያለውን የአፈር ለምነት ችግር መቀነስና ምርታማነትን መጨመር እንደሆነ ገልጸው ስልጠናው ከዚህ ቀደም ከነበሩት ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገው ሰልጣኙን አሰልጥኖ መስደድ ብቻ ሳይሆን የተመረተውንም ቨርሚ ኮምፖስት አርሶ አደሩ ድረስ በመውሰድ ማሳው ላይ ተግባራዊ የሚያደርግበት ተግባር ተኮር ስልጠና እንደሆነ ተናግረዋል።
ስልጠናው ላይ ያነጋገርናቸው ሞዴል አርሶ አደሮች እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው የሚያደርገው ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ድጋፉ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።