የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ደራሲ የዝና ወርቁ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከመምህራን እና ተማሪዎች ጋር ተወያዩ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 14/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ስራ አስኪያጅ ደራሲ የዝና ወርቁ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከመምህራን እና ተማሪዎች ጋር ትምህርታዊ ውይይት አካሄዱ። ደራሲ የዝና ወርቁ በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ዘመናዊ አጭር ልቦለድ ደራሲ ሲሆኑ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ እና በልዩ ልዩ ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ ሆነውም ሰርተዋል።
በዩኒቨርሲቲው ማኅበራዊ ሳይንስ እና ሥነ -ሰብዕ ኮሌጅ የአማርኛ ቋንቋና ሥነ- ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ያሰናዳው ይህ ትምህርታዊ ውይይት ዛሬ በ"LH4" ሴሚናር አዳራሽ የተካሄደ ሲሆን መምህራን፣ ተማሪዎች እና የሥነ-ጽሁፍ አድናቂዎች ታድመውበታል።
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የማኅበራዊ ሳይንስና ሥነ- ሰብዕ ኮሌጅ ምክትል ዲን እና የዲኑ ተወካይ መምህር ይሄይስ ባንታየሁ፤ ትምህርት ክፍሉ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ደራሲያን እና ጋዜጠኞችን እየጋበዘ ልምዳቸውንና ተሞክሯቸውን እንዲያካፍሉ ሲያደርግ እንደነበር አውስተዋል።
ዛሬ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ባለሙያ የሆኑትን ደራሲ የዝና ወርቁ መጋበዙ ትልቅ ስራ ነው ያሉት መምህር ይሄይስ፥ የውይይት መድረኩ በዩኒቨርሲቲው መካሄድ ለተማሪዎች ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት ምን አይነት ትጋት እንደሚጠበቅባቸው አስቀድመው እንዲያውቁና እንዲዘጋጁ ልምድ የሚሰጣቸው ነው ብለዋል።
በውይይት መድረኩ የደራሲ የዝና ወርቁ አጭር ግለ-ታሪክ መግለጫ በትምህርት ክፍሉ መምህር እንግዳወርቅ እንድሪያስ ቀርቧል። በደራሲዋ መፃህፍት ሀሳቦች ላይ ያተኮረ ዳሰሳ ደግሞ ሃሳብ ደግሞ በመምህር ቴዎድሮስ ቦጋለ ቀርቧል።
መምህር ቴዎድሮስም ደራሲ የዝና ወርቁ በአማርኛ ሥ-ጽሁፍ ታሪክ የዘመናዊ አጭር ልቦለድ የመጀመሪያዋ ሴት ደራሲ ይሁኑ እንጅ ከቀደምት የአጭር ልቦለድ ስራዎች በኋላ የዘመናዊ አጭር ልቦለድ ወጣኒያን ከሆኑትም ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ለውይይት መነሻነት የቀረበውን ዳሰሳ ተከትሎ ለደራሲዋ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከታዳምያን የተነሱ ሲሆን፣ ደራሲ የዝና ወርቁም ለተነሱት ጥያቄዎችና ሀሳቦች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ደራሲዋ፦ በተለይም የቋንቋና ሥነ-ጽሁፍ እንዲሁም የጋዜጠኝነት ተማሪዎች በንባብ እና ፅሞና አስተሳሰባቸውን እና የወደፊት ሙያዊ ህይወታቸውን ማዳበር አለባቸው ብለዋል። ንባብና ፅሞና ነገሮችን የምንረዳበትን እና ለሚያነቡን፣ ለሚሰሙን የምናስረዳበትን እውቀት ያጎለብቱልናል የወደፊት ደራሲዎችና ጋዜጠኞች ደግሞ ይህን ማዳበር አለባችሁ ነው ያሉት ደራሲ የዝና ወርቁ።
ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሁፍ እድገት ደካማ መሆን አንዱ ክፍተት ሥነ-ጽሁፍን በሚገባ የሚበይኑ ሃያሲያን በበቂ አለመኖር መሆኑን ያነሱት ደራሲ፤ ተማሪዎች ደራሲነት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ሃያሲነትም ለሥነ-ጽሁፍ ማደግ ያለውን አስተዋፅኦ ተገንዝባችሁ እራሳችሁን ለዘርፉ አዘጋጁ ብለዋል።
በውይይቱ ማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የአማርኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ሀብታሙ መስፍን በበኩላቸው፤ የውይይት መድረኩ የታሰበውን ዓላማ ያሳካና ብዙ ልምዶች የተወሰዱበት እንደነበር ገልጸዋል።
በተለይም ደራሲዋ በሀገራችን የመጀመሪያዋ ሴት የዘመናዊ አጭር ልቦለድ ደራሲ እንደመሆናቸው ለአጭር ልቦወለድ አፃፃፍ ትምህርት በተግባር ለማሳየት ውይይቱ ትልቅ ድጋፍ የሚሰጥ ነው ብለዋል መምህር ሀብታሙ።
በውይይቱ መጨረሻ ደራሲ የዝና ወርቁ የደረሷቸውን መፅሐፎች ለኮሌጁ በስጦታ መልክ ያበረከቱ ሲሆን፥ በዘንድሮ ዓመት የጋራ ኮርሶቸውን አጠናቀው ወደ ትምህርት ክፍሉ አዲስ ለተቀላቀሉ ተማሪዎች ደግሞ የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባባል ደርጎላቸዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ