ዲላ ዩኒቨርሲቲ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር በሰጠው መሬት ላይ በምርምር ያለማውን የእንሰት ችግኝ ለአርሶ አደሮች አሰራጨ

ዲ.ዩ፦ መጋቢት 22/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በሳይንሳዊ መንገድ የበለጸጉ የእንሰት ችግኞችን በጌዴኦ ዞን ሁለት ወረዳዎች ውስጥ ለተመረጡ አርሶአደሮች አሰራጭቷል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ኘሬዝዳንት ደረጄ ክፍሌ (ዶ/ር)፤ በምርምር ለምቶ ለአርሶአደሮች የተሰራጨው የእንሰት ችግኝ በዩኒቨርሲቲው ተደራሽ ከሚደረጉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው ብለዋል። ዲላ ዩኒቨርስቲ የአከባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ በማሻሻል ገቢውን ለማሳደግ ተመሳሳይ በርካታ ስራዎችን መስራቱንም ገልፀዋል።
በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ፣ ገደብ እና ቡሌ ወረዳዎች የአርሶአደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ፣ ሳይንሳዊ ሂደታቸውን የጠበቁና በምርምር የበለጸጉ የእንሰት ችግኞች የማዘጋጀት ስራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ በይርጋጨፌ እና ገደብ ወረዳዎች የተዘጋጁት ችግኞች በወረዳዎቹ ለተመረጡ አርሶ አደሮች መሰራጨታቸውን ነው የገለፁት ም/ፕሬዝዳንቱ።
እርሳቸው አክለውም፤ የተሰራጨው የእንሰት ችግኝ በአጭር ጊዜ የምግብ ዋስትናን ከማስጠበቁ በላይ ችግኙን ገዝተው ማልማት ለማይችሉ እንዲሁም ለውስን ሞዴል አርሶአደሮች ተደራሽ መሆኑንም ገልፀዋል።
ስለሆነም በይርጋጨፌ ዶማርሶ ሳይት ሁለት ሺህ 500 እና በገደብ ወረዳ ሀሎ በርት ሳይት አራት ሺህ የእንሰት ችግኝ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ሶስት ሺህ ችግኞች ለአርሶአደሮች እንዲሁም አንድ ሺህ ችግኞች ደግሞ ለተቋማት መሰራጨታቸው ተነግሯል።
በቡሌ ወረዳ የለማው የእንሰት ችግኝ በአንፃሩ በውርጭ ምክንያት ለጊዜው ለስርጭት ያልደረሰ መሆኑን የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ደረጄ አያይዘው ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ታደሰ በበኩላቸው፤ ከይርጋጨፌ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ለተወጣጡ 48 አርሶአደሮች ለእያንዳንዳቸው አርባ የእንሰት ችግኞች መታደሉን፤ በተመሳሳይ ከገደብ ወረዳ አራት ቀበሌዎች ለተመረጡ 60 አረሶአደሮች ደግሞ ለእያንዳንዳቸው 50 የእንሰት ችግኝ መከፋፈሉን ተናግረዋል።
አርሶአደሮች በምርምር ማዕከሉ የተገነዘቡትን የእንሰት አያያዝና አተካከል በመረዳት በማሳቸው ያሉትን የእንሰት ችግኞች በተሻለ አያያዝ በመንከባከብ የምግብ ዋስትናቸውን እንዲያረጋግጡ አቶ ተካልኝ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ፍቅሩ ታምሩ በማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት የእንሰት ኘሮጀክት አስተባባሪ፤ ምንም እንኳን ሳይንሳዊ ምርምር ተደርጎ እውቅና ባያገኙም በጌዴኦ ዞን ውስጥ ሠላሳ ሁለት የእንሰት ዝርያዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከእነዚህ ውስጥ አርሶአደሮች አስራ ዘጠኝ የሚደርሱ የእንሰት ዝርያዎችን በመጠቀም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። የምርምር ማዕከሉም በአሁን ሰዓት አስራ አራት የእንሰት ዝርያዎችን በማባዛት ስርጭት ማድረጉን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ፍቅሩ ገለፃ በርካታ በመመናመን ላይ የነበሩ የእንሰት ዝርያዎችን ከአርሶአደሮች ጓሮ በመሰብሰብና ወደ ማዕከሉ በማምጣት የተባዙ እንደሆኑና መሰል ስራዎችን ወደፊትም ለመስራት ታቅዷል።
በእንሰት ችግኞች ስርጭት መርሃግብሩ ላይ የተገኙት የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዮት ደምሴ በበኩላቸው፤ በዞኑ ቡና እና እንሰት ለአርሶአደሩ የህይወት ዋስትና በመሆኑ በእያንዳንዱ አርሶአደር ጓሮ መቶ የእንሰት ችግኞችን በየአመቱ በመትከል፣ በአምስት ዓመት ውስጥ የዞኑ አርሶአደር ከእራሱ አልፎ ለአከባቢው ማህበረሰብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲችል እየሰራን ነው ብለዋል።
አቶ አብዮት አክለውም፤ "የጋራ ጠላታችን በሆነውና በጋራ ልንዘምትበት በሚገባን ድህነትን ታሪክ የማድረግ ርብርብ የዲላ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ያለው የምርምር ስራ ሚናው ከፍተኛ በመሆኑ አጠናክሮ ይቀጥል" ሲሉ አሳስበዋል።
የገደብ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኤርምያስ አቢዲዩ በንግግራቸው፤ ዩኒቨርሲቲው የአርሶአደሮችን ህይወት ለመለወጥና የምግብ ዋስትናቸውን በእራሳቸው ማሳ ላይ እንዲያረጋግጡ ለማስቻል በምርምር በማገዝ እያደረገ ያለው አበርክቶት የተቋሙን የህዝብ ወገንተኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የእንሰት ችግኝ ለመውሰድ ከተመረጡት አርሶአደሮች መካከል አቶ ንዋይ ዋቆ እና ወ/ሮ አረጋሽ አራቦ በሰጡን አስተያየት፤ የእድሉ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልፀው፤ የአካባቢውን አርሶአደሮች ህይወት ለመለወጥ ዲላ ዩኒቨርሲቲ እያደረገ ያለው እገዛ የሚደነቅ ነው ብለዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን