የአኘል ምርት በቡሌ ወረዳ የሚገኙ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው

ዲ.ዩ: መጋቢት 26/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት የአኘል ምርት በቡሌ ወረዳ የሚገኙ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ገልጿል።
አቶ ተካልኝ ታደሰ የዳሬክቶሬት ፅ/ቤቱ ዳይሬክተር እንደገለጹት፤ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ስር ተደራሽ ከሚደረጉ ኘሮጀክቶች መካከል የመካከለኛውና የደጋማ አከባቢዎችን የሚሸፍነው የድንች፣ ቀርቀሃ፣ እንሰትና አኘል ልማት ናቸው ብለዋል።
አሁን ላይ በትኩረት እየተሰራ ያለው የአኘል ምርት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ የጌዴኦ ዞንና አከባቢው በብዛት የሚታወቅበት የቡና ምርት በይበልጥ በወይናደጋው እና ቆላ አካባቢ በመሆኑ የደጋውን አካባቢ ደግሞ በአኘል ምርት ታዋቂ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ አኘል ምርት ላይ በመስራት በየእያንዳንዱ አርሶ አደር ጓሮ የአኘል ዛፍ እንዲኖርና ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል። በተመሳሳይ በአፕል ምርት የዩኒቨርሲቲውን የውስጥ ገቢ የማመንጨት ስራ ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም አቶ ተካልኝ አያይዘው አንስተዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የአኘል ኘሮጀክት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አብዲ አደም፤ አኘል መገኛው እስራኤል ሲሆን ወደ ሀገራችን የገባውው በ1952 ዓ.ም በካቶልካዊያን በኩል ጨንቻ (አርባምንጭ አካባቢ) ነው ብለዋል። እንዲሁም ወደ ቡሌ ወረዳ የመጣው በ1994 ዓ/ም "ዘላቂ የመሬት አያያዝ ኘሮጀክት" ላይ በሚሰራ ግብረሰናይ ድርጅት በኩል መሆኑን አስረድተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲም በ2004 ዓ.ም ይህን ኘሮጀክት በማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ምርምር ስር በማካተት፤ ከጨንቻ ችግኞችን በማምጣት ለአርሶ አደሮች ሲያሰራጭ መቆየቱ ተገልጿል።
በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ችግኙን በዩኒቨርሲቲው የምርምር ማዕከልና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ በማባዛት የአከባቢውን ማህበረሰብ ተጠቂሚ ማድረግ መቀጠሉን አቶ አብዲ አንስተዋል።
ተመራማሪው አክለውም፤ በዚህም ሂደት ካሉት ሰባት (7) የአፕል ዝርያዎች ውስጥ የተሻለ ምርት የሚሰጠው በመለየቱ ምርታማነትን ለማሳደግ አይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል። ዛሬ ላይ በወረዳው የአኘል ምርት 40 ሄክታር የደረሰ ሲሆን ይህን ቁጥር ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአኘል ምርት ተጠቃሚ ከሆኑት አርሶአደሮች መካከል አቶ ምትኩ ጎበና እና አቶ ጀማል ከድር በበኩላቸው፤ በማሳቸው ከ230 በላይ የአኘል ዛፍ መኖሩን ገልጸው፣ አንዱ ዛፍ ምርት ሲይዝ ከ120 እስከ 150 ኪ.ግ እንደሚሰጥ ገልፀዋል። የአፕል ምርታቸውን በመሸጥ በአመት እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር (100,000) ገቢ እንደሚያገኙም ገልፀዋል።
ለዚህ ውጤት የመብቃታቸው ሚስጥር ዲላ ዩኒቨርስቲ በስልጠና እንዲሁም ችግኝ በማቅረብ እገዛ ስላደረገላቸው መሆኑን አስገንዝበዋል።
አርሶአደሮቹ በቀጣይም ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ማድረጉን እንዲያጠናክር የጠየቁ ሲሆን፣ በአፕል ምርት ያገኘቱን ውጤታማነትም ለማስፋት ለአካባቢው አርሶአደሮች የልምድ ልውውጥ በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸውልናል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን