ዲ.ዩ፦ ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክቶሬት በጌዴኦ ዞን ቡሌ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የቀረቀሃ ችግኝ ስርጭት አካሂዷል።
ደረጄ ክፍሌ (ዶ/ር) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ኘሬዝዳንት፤ ከአምስት አመታት በፊት ጀጎ ላይ የነበረው የቀርቀሃ ደን የመጥፋት አደጋ አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰው፤ ደኑን መልሶ ለማልማት የአምስት አመት ኘሮጀክት በመንደፍ ወደ ስራ በመገባቱን አሁን ላይ ወደ 4.5 ሄክታር የቀርከሃ ደን መልሶ ማልማት ተችሏል ብለዋል።
ዶ/ር ደረጄ አክለውም፤ በዚህ ስራ 407 አርሶ አደሮች የቀርቀሃ ችግኝ በማሳቸው እንዲያለሙ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል ነው ያሉት። አያይዘውም ከራሳቸው አልፎ ለሌሎች አርሶ አደሮች ግንዛቤ በመፍጠርና በጓሯቸው የሚያለሟቸውን የቀርቀሃ ችግኞች ለማዳረስ እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የአሁኑ የቀርቀሃ ችግኝ ስርጭት የመጨረሻ ዙር ስርጭት መሆኑን ዶ/ር ደረጄ ገልጸው፤ የወረዳው ግብርና ቢሮ አገር በቀል ዛፎችን እንደ ኮሶ፣ ጽድ፣ ወይራ የመሳሰሉትን እያለማ ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እንቅስቃሴ መጀመሩንም አያይዘው ጠቁመዋል።
አቶ ተካልኝ ታደሰ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር በበኩላቸው፤ የዲላ ዩኒቨርሲቲ በ2008 ዓ.ም ደኑ መውደሙን ተመራማሪ መምህራን ቦታው ድረስ በመሄድ ካረጋገጡ በኋላ፤ ባለፉት አምስት አመታት ችግኞችን በማፍላት፣ በማሰራጨት ደኑን በመታደግ ወደነበረበት መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለት ከሰባት ቀበሌዎች ለተውጣጡ ሰማንያ አምስት (85) አርሶ አደሮች ለእያንዳንዳቸው እንደ መሬታቸው ይዞታ ከ500 አስከ 1000 የቀርቀሃ ችግኞች ለማሰራጨት ታስቦ አንድ መቶ ሺህ (100,000) ችግኞች ለስርጭት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል። ዩኒቨርሲቲው በአምስት አመት ውስጥ ለማሳካት አቅዶ የተነሳነውን ሙሉ በሙሉ ማሳካቱንም አቶ ተካልኝ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል አቶ ዮሐንስ ታደሰ፣ የጌዴኦ ዞን ደንና አከባቢ ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ በበኩላቸው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በአካባቢው የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት በምርምር ድጋፍ እያደረገ መቀጠሉን ገልጸዋል። ይህን የቀርቀሃ ደን ወደ ነበረበት ለመመለስ የተሰራው ስራ ትልቅ አሻራ ያለው ነው ብለዋል።
የቀርቀሃ ችግኝ ሲወስዱ ያገኘናቸው አቶ ብርሃኑ ኩርሴ እና አቶ አሰፋ ጀጎ፤ ጠፍቶ የነበረው የቀርቀሃ ደን "ተመልሶ በዚህ መልኩ እናገኛለን ብለን አስበን አናውቅም ነበር" ሲሉ ደኑ መልሶ ያገግማል የሚል ተስፋቸው ተሟጦ እንደነበር ገልጸውልናል። ይሁን እንጅ ደኑን መልሶ ህያው ለማድረግ ዲላ ዩኒቨርሲቲው የሰራው ስራ የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ
ተክክለኛ እና ወቅታዊ ተቋማዊ መረጃ ለማገኘት
#ቴሌግራም፦ University of the Green Land
ይከታተሉን!
ለጥያቄና አስተያየተዎ
#ኢሜይል፦ pirdir@du.edu.et
ይላኩልን