ዲላ ዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናን ለመተግበር የሚያስችል የ"ኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርአት አበለፀገ

ዲ.ዩ፦ ሚያዚያ 12/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ከያዝነው 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ይሰጣል ተብሎ እቅድ የተያዘለትን የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች የመውጫ ፈተናን ለመተግበር የሚያስችል የ"ኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርአት ማበልፀጉን ዲላ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የ"ኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርአቱ (Online Examination Management System) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ መምህራን በልፅጎ የዩኒቨርሲቲው ማኔጀመንት አባላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የከፍተኛ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና እንዲወስዱ በተወሰነው መሰረት ፈተናው የተሳካ እንዲሆን ዲላ ዩኒቨርሲቲ ዘርፍ ብዙ ዝግጅት እያደረገ ነው ብለዋል።
ለመውጫ ፈተና ልምምድ የሚውል የኮምፒውተር ስርአት እንዲዘጋጅ ሶስት የኮምፒውተር ሳይንስ መምህራንን ያቀፈ ቡድን በአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት በኩል ተቋቁሞ በአንድ ወር የጊዜ ገደብ ውስጥ ስርአቱን እንዲያበለፅጉ በተሰጠው የስራ መምሪያ መሰረት ተሰርቶ መቅረቡን ዶ/ር ችሮታው ገልጸዋል።
የ"ኦንላይን" ፈተና አስተዳደር ስርአቱን ካቀለፀጉት መምህራን መካከል የሆኑት አቶ ነጋ ተፈራ የበለፀገው ስርአት ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ አሰራሮችና አጠቃቀሞች አስመልክቶ ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት አባላት ገለፃ ሰጥተዋል።
አቶ ነጋ፥ በአገር አቀፍ ደረጃ የመውጫ ፈተና ሲቀመጡ ተማሪዎች በ'ኦንላይን' ፈተና መውሰድ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመደናገጥና የመደናገር ችግር እንዳይገጥማቸው በማሳብ በማኔጅመንቱ ኃላፊነት ከተሰጠን ቀን ጀምሮ በትጋት በመከወን ስርአቱን አበልጽገን አስረክበናል ብለዋል።
የ"ኦንላይን" ፈተና አሰተዳደር ስርአቱ ከበላይ አመራሮች ጀምሮ የኮሌጅ ዲኖች፣ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ መምህራን እንዲሁም ተማሪዎች የተፈቀደላቸውን ስራ እንዲከውኑበት ተደርጎ የበለጸገ ነው ብለዋል አቶ ነጋ።
የዱላ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት አባላትም ስርአቱ ላይ ሊገጥሙ ይችላሉ ያሏቸውን የደህንነት እና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ያነሱ ሲሆን አቶ ነጋ ተፈራ ስርአቱ አስፈላጊውን የደህንነት ፍተሻ ተደርጎበት፣ የጥንቃቄ ስርአቶችም ተሟልተውለት መበልፀጉን አብራርተዋል።
አቶ ነጋ ተፈራ አክለውም፤ የስርአቱን አጠቃቀም የተግባር ልምምድ ለበላይ አመራሮች እና ኮሌጅ ዲኖች መስጠት መጀመራቸውን እንዲሁም ለትምህርት ክፍል ኃላፊዎች፣ ለመምህራን እና ተማሪዎች በቅርቡ ስልጠናዎች እንደሚዘጋጅላቸው ጠቁመዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ