የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውሮ ተመልክቷል

ዲ.ዩ፦ ግንቦት 04/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) የተመራ ከፍተኛ የአመራር ቡድን በተቋሙ እየተከናወኑ ያሉ ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ስራዎችን ጎብኝቷል።
በከፍተኛ አመራሩ ምልከታ መጀመሪያ በኦዳያአ ግቢ እየተሰራ ያለ የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ ደህንነት፣ የተማሪዎች እና ሰራተኞች አገልግሎት አሰጣጥ የሚመለከቱ ዘርፎችን ደህንነትና መረጃ አያያዝ የሚያዘመንን የአይ.ሲቲ መሰረተ ልማት (Security Operation Center) ተጎብኝቷል።
በዘርፉ የግቢውን ድህንነት ለመጠበቅ፣ የተማሪዎች እና ሰራተኞችን መረጃ ለመቆጣጠርና እንደ ምግብ ቤት፣ ሬጂስትራር እና መሰል ከተማሪዎች አገልግሎት ጋር የተያያዙ ዘርፎችን የመረጃ ስርአት በተቀናጀ መልኩ ለማስተዳደር የሚረዱ የአይ.ሲቲ ልማቶች ያሉበት የአፈፃፀም ደረጃ ምልከታ ተደርጎባቸዋል።
በመቀጠል አመራሩ በእፅዋት ጥበቃ እና ኢኮቱሪዝም ማዕከል እየተከናወኑ ያሉ ልዩ ልዩ የ"ፋሲሊቲ" ስራዎችም ጎብኝቷል። በማዕከሉ የጎብኝዎችን የቆይታ ጊዜ ለማሻሻል፣ ምቹ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች ያሉበት ደረጃ ተቃኝቷል። እንደ ቤተሙከራ እና መሰል ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ያሉ ስራዎች በቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ከሁለቱ ምልከታዎች ቀጥሎ በግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ስር ሰፊ ትኩረት ተሰጥቶት እየተከናወነ ያለውን የዶሮ እርባታ ልማት ተጎብኝቷል። በጣቢያው እየተከናወኑ ያሉ የዶሮ እርባታ ስራዎች ከኮሌጁ እና ከጣቢያው አስተባባሪዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።
ጣቢያው በተሻለ ሁኔታ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ዶሮ እና እንቁላል የማቅረብ ስራውን በበለጠ አስፍቶ ለመስራት እንዲረዳ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር የፈቀዱለትን የግብአት ግዢዎች በቅርቡ ፈፅሞ ወደ ተሻለ ስራ እንዲገባ ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ችሮታው አየለ አሳስበዋል።
በአመራሩ መልከታ የተደረገበት ሌላኛው ፕሮጀክት የህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ከነባሩ ሆስፒታል ህንፃዎች እድሳት ጋር በተያያዘ እየተከናወኑ ያሉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ናቸው። በእድሳቱ በመጠናቀቅ ላይ ያሉ ህንፃዎች እና አሁን እየተሰሩ ያሉ ግንባታዎች ምልከታ ተደርጎባቸዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር) ምልከታ በተደረገባቸው መሰረተ ልማቶች የተስተዋሉ መልካም ውጤቶችን እና ተግባራትን አበረታትተው በተሻለ መልኩ ትኩረት ተሰጥቷቸው እንዲሰፉና ተቀላጥፈው እንዲሰሩ ለፕሮጀክቶቹ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች አደራ ብለዋል።
በእያንዳንዱ ምልከታ በተደረገባቸው ፕሮጀክቶች የታዩ የአፈፃፀም ክፍተቶችና መጓተቶች በልዩ ትኩረት እንዲሻሻሉ፣ በየስራዎቹም የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው የስራ ክፍሎች ድርሻቸውን በተገቢው ሁኔታ ተወጥተው፣ ፕሮጀክቶቹ በተጠበቀው ጊዜ ተጠናቀው በሙሉ አቅም ወደ ስራ እንዲገቡ ዶ/ር ችሮታው መመሪያ ሰጥተዋል።
በቀጣይ ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠላቸው አቅጣጫ መሰረት ተጠናቀው በሙሉ አቅም ወደ ስራ እንዲገቡ በሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው የስራ ክፍል አመራሮች እና በፕሬዝዳንቱም ጭምር በቅርበት ክትትል ይደረግባቸዋል ተብሏል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ