ዲ.ዩ፦ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ"ደረጃ ዶት ኮም" ጋር በመተባበር ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች ለተመረጡ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል። እነዚህ መምህራን በቀጣይ ለሚመረቁ ተማሪዎች የቅጥር እና የስራ ዝግጁነት ክህሎት የሚያሰለጥኑ መሆኑ ታውቋል።
ደሳለኝ አዳሙ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና የስነ ውጤት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፤ የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት ስለ ስራ አፈላለግ ራሳቸውን ቀድመው ከስራ ጋር ሊያዛምዱ የሚችሉባቸውን የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠት በዩኒቨርሲቲያችን መምህራኖችን ቀድሞ በማሰልጠን፤ የሰለጠኑ መምህራን ደግሞ በቀጣይ ተመራቂ ተማሪዎቻችንን እንዲያሰለጥኑ በማሰብ የተሰጠ የአሰልጣኞች ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ አያይዘው፤ ተማሪዎች ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት በስራ ዓለም ላይ ስላሉ ነገሮች ግንዛቤ ሳይኖራቸው ሊወጡ ይችላሉ ብለዋል። በመሆኑም ይህ ስልጠና ከመሰል ችግሮች ተማሪዎችን የሚታደግና በተሻለ ግንዛቤ ወደ ስራ ዓለም እንዲቀላቀሉ የሚያስችሉ የተለያዩ ልምዶች፣ ችሎታንና በራስ መተማመን የሚያስችል መሆኑን ዶ/ር ደሳለኝ አክለው ገልጸዋል።
ስልጠናውን የሰጡት የ "ደረጃ ዶት ኮም" የአሰልጣኞች አሰልጣኝ አቶ ነብዩ ዳንኤል እና የ "ደረጃ አካዳሚ" አሰልጣኝ አቶ አቤሴሎም ሳምሶን በበኩላቸው፤ ስልጠናው ከተለያዩ ትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ መምህራን ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ለተመራቂ ተማሪዎች ስለ ስራ ዝግጁነት ማሰልጠን በሚችሉበት ደረጃ የሚያግዛቸው ነው ብለዋል።
አሰልጣኞች አክለውም፤ የዩኒቨርሲቲው መምህራን ያላቸውን ተመራቂ ተማሪዎች አሁን ባለው የስራ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚያስፈልጉ የስራ ዝግጁነት ክህሎትና እውቀት ላይ በማብቃት ደረጃ እንዲያውቁ የማድረግ ዓላማ እንዳለው አንስተዋል፡፡
የአሰልጣኞች ስልጠና ሰልጣኝ እንዲሁም አስተባባሪ መምህርት ትዕግስት አበባው፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት ትምህርት ክፍል መምህርት እና የስነ ውጤት ምክትል ዳይሬክተር እንደገለጹት፤ ይህ ስልጠና ተመራቂዎች በገበያው ላይ እንዴት ራሳቸውን ብቁ እና ተወዳዳሪ አድርገው ከሌሎች በተሻለ የተቀጣሪነት እድላቸውን በሚያሰፋላቸው አኳኋን የምናሰለጥናቸው ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
አቶ ተሾመ መለሰ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ዜጋ እና ስነ ምግባር ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር በበኩላቸው፤ ስራና ሠራተኛውን በማገናኘት እንዲሁም ቀጣሪ ድርጅቶች ከተመራቂ ተማሪዎች ጋር ማስተሳሰር በተመለከተ ያለውን ክፍተት በትክክል ያሳየ ስልጠና እንደነበር ጠቅሰዋል።
ይህንን ስልጠና የሰጠው "ደረጃ ዶት ኮም" ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር ተመራቂ ተማሪዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ለማስተሳሰርና የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን ለመስጠት ከዚህ ቀደም የጋራ ስምምነት መፈራረሙ የሚታወስ ነው።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ