የባዮጋዝ ልማት ስሥራዎችን የመገምገምና የመከታተል ስራ ተካሄደ

ዲ.ዩ፦ ሰኔ 30/2015 ዓ.ም( ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጀንስ ጋር በመተባበር በጌዴኦ ዞን በወናጎና በይርጋጨፌ ወረዳዎች እየተገበረ ያለውን የባዮጋዝ ልማት ስራዎች ክትትልና ግምገማ ተደረገ።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት፤ የባዮጋዝ ኘሮጀክቱ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንስ ጋር በመተባበር እንደሚሰራ ገልጸው፤ ማዕዲንና ኢነርጂ ዘጠኝ ሚሊየን፣ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ሁለት ሚልየን እንደሚሸፍኑ አብራርተዋል። ቀሪው ደግሞ ከተጠቃሚው ማህበረሰብ በግብዓት መልክ የሚሰበሰብ ሆኖ በአጠቃላይ 13 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው ተብሏል።
ይህን መሰል ፕሮጀክቶች በሌሎች የአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች በስፋት እየተሰራ ያለ መሆኑን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፤ የእኛ ፕሮጀክት ጅምር ስራ እንደመሆኑ መጠን 150 አባወራዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ማህበረሰቡ ቴክኖሎጂውን በአግባቡ እንዲጠቀም ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ፣ እናቶች ለጭስና መሰል ተያያዥ የጎንዮሽ ችግሮች ሳይጋለጡ ምግብ የማብሰልና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያለመ ነው ብለዋል።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም ባለፉት ጊዜያት የአካባቢው ማህበረሰብ ምግብ ለማብሰልም ሆነ ሌሎች ግልጋሎቶችን ለማግኘት እንጨትን ለማገዶነት እንደሚጠቀም ገልጸው፤ መሰል ድርጊቶች የአካባቢው ሥነ-ምህዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለሚያደርሱ፤ ይህን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ችግሩን መፍታት ይቻላል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር፤ ከባዮጋዝ የሚወጣውን ተረፈ ምርት የተፈጥሮ ማዳበርያ አድርጎ መጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ኘሮጀክቱ የምግብ ዋስትናችንም ላይ ሆነ ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት ብለዋል።
ኘሮጀክቱ አሁን ላይ 75 በመቶ ያክል የተጠናቀቀ መሆኑንና በቀጣይ ወራት ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። ለዚህ ፕሮጀክት ለተሳተፉና አስተዋጽኦ ላበረከቱ የክልል፣ የዞንና የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳሬክቶሬትን አመስግነዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ ተመስገን፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት በበኩላቸው፣ በማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰሩ ስራዎች በዋናነት በውስጥ በመደበኛ በጀት ላይ ብቻ መሰረት ያደረጉ እንደነበሩ ተናግረው፤ የማህበረሰብ አገልግሎት ፍላጎት ሰፊ እደመሆኑ መጠን ሁሉም የሙያ ዘርፎች የራሳቸውን አበርክቶ ማበርከት ቢፈልጉም በቂ የሆነ የገንዘብ ምንጭ አልነበረም ብለዋል። ሆኖም ይህን የማህበረሰብ ፍላጎት ለማርካት ከአጋር ድርጅቶች ጋር መስራት አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል።
እንደ ዶ/ር ሀብታሙ ገለጻ፣ ከደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንስ ጋር የተሰራው ስራ፣ ክትትልና ግምገማ የባዮጋዝ ግንባታ አንዱ ከውጭ አጋር ድርጅቶች ጋር መሰራት ያለብን ስራ ማሳያ ነው ብለዋል። የዚህ ኘሮጀክት አብዛኛውን ስራ የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንስ እየሰራ ሲሆን፣ ዩኒቨርሲቲው ለግንባታው 750 ኩንታል ሲሚንቶ ለማቅረብ የገባውን ውልም መፈፀሙን ገልጸዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ አክለውም፤ በሁለቱ ወረዳዎች ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የቀረቡት ግብዓቶች ሳይበላሹ ኘሮጀክቱ በታለመለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አሳስበዋል።
የደቡብ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ኤጄንስ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛ በበኩላቸው፤ በጌዴኦ ዞን በሁለት ወረዳዎች ላይ 150 አባዎራዎች የባዮጋዝ ተጠቃሚ ለማድረግ ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመው ወደ ሰራ መገባቱን አስታውሰው፤ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ባለፉት ጊዜያት ሰፊ ስራ የተሰራ ቢሆንም ከማህበረሰብ አገልግሎት አንጻር የዘንድሮው በከፍተኛ ሀኔታ የተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ ወ/ሮ አፀደ ገለጻ፤ በተለይ የእናቶችን የስራ ጫና ከመቀነሱም በላይ ጤናቸው ተጠብቆ እንዲኖሩ ያግዛል ብለዋል። ይህ ባዮጋዝ ሦስት አገልግሎት ያለው ሲሆን የምድጃ፣ ማብራትና የተፈጥሮ ማዳበርያን ለመጠቀም እንደሚያስችል ገልጸዋል።
አሁን ላይ ከታቀደው150 አባዎራዎች ለ50 ሰው የተጠናቀቀ ሲሆን 30 ወደ አገልግሎት የገባ፣ 20 ደግም ግንባታው አልቆ የእበት ሙሌት ስራ እየተሰራ መሆኑን እንዲሁም እስከ ሐምሌ 30/2015 ዓ.ም ድረስ እንደሚጠናቀቅ አያይዘው ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ አለሚቱ በቀለና ወ/ሮ ንጋቷ አለሙ በበኩላቸው፤ ባለፉት ጊዜያት የማብሰያውም ሆነ የመብራት ችግር ከፍተኛ እንደነበረ ገልፀው፤ አሁን ይህን ቴክኖሎጂ መጠቀም በመጀመራቸው የጓሮ አትክልቶችን ለማልማት ተረፈ ምርቱ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ