ለቅድመ ምረቃ እጩ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተና ዛሬ መሰጠት ጀምሯል

ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 03/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለቅድመ ምረቃ እጩ ተመራቂዎች በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀውን አገር አቀፍ የመውጫ ፈተና በዛሬው እለት መስጠት ጀምሯል።
ታምራት በየነ (ዶ/ር፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተማሩበት የትምህርት መስክ ከፍተኛ ግንዛቤ ያላቸውንና በራሳቸው የሚተማመኑ ተመራቂዎችን ለማፍራት ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ ከነዚህ መካከል አንዱ የመውጫ ፈተና መስጠት እንደሆነ ገልፀዋል።
ዶ/ር ታምራት አክለው፤ ፈተናው በኦንላይን በተሳካ መልኩ እንዲሰጥ ዩኒቨርሲቲው በቂ ዝግጅት በማድረግ ተማሪዎች ሁለት ጊዜ በዩኒቨርሲቲው የተዘጋጀ፣ እንዲሁም ሁለት ጊዜ ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጁ ሞዴል ፈተናዎች በመሰጠቱ በቂ ልምድ ተገኝቷል ብለዋል።
ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መርሃግብር መሰረት 1668 የዲላ ዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂዎች፣ 835 ከግል ትምህርት ተቋማት የመጡ እጩ ተመራቂዎች፤ በአጠቃላይ 2503 እጩ ሙሩቃን መውጫ ፈተናውን እንደሚወስዱ ተናግረዋል።
ዛሬ ጧት በነበረው የፈተና መርሃግብር ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ለፈተና መቀመጥ ከነበረባቸው ከአራት የትምህርት አይነት ከተወጣጡ 216 ተማሪዎች ውስጥ ሁሉም ፈተናውን በመውሰድ 100% አፈፃፀም ተመዝግቧል።
በአንፃሩ በተመሳሳይ በዛሬ ጧት መርሃግብር ከሁለት የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፈተናውን እንዲወስዱ ከተመደቡ 35 ተማሪዎች መካከል ከአንድ ተማሪ በስተቀር 34 ተማሪዎች ተፈትነዋል።
ፈተናውን ለሚወስዱ አጠቃላይ ተማሪዎች መልካም ፈተና እንመኛለን!
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ