ለመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው አገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ተጠናቀቀ

ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 07/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመራቂ ተማሪዎች ሲሰጥ የነበረው የመውጫ ፈተና ዛሬ ተጠናቋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲም የፈተናውን ደህንነትና ሚስጥራዊነት በማስጠበቅ እረገድ ትኩረት ሰጥቶ ከፀጥታ ግብረ-ኃይሉ ጋር በመቀናጀት ፈተናውን ሰጥቷል። ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መርሃግብር መሰረትም ከአንድ ሽህ 600 በላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ከ870 በላይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እጩ ተመራቂዎች የመውጫ ፈተናውን ተፈትነዋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር )፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት፤ በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጁ የፈተና ማዕከላት ከሰኔ 30 ጀምሮ ሲሰጥ የቆየው የመውጫ ፈተና በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በፈተናው ወቅት እንደችግር ተከስቶ የነበረው ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመጡ ተማሪዎች መካከል ለማስፈተን በነበረው ሂደት ውስጥ የኮምፒውተር አጠቃቀም ክህሎት የሌላቸው እና የይለፍ ቃላቻውን የሚረሱ አጋጥመው እንደነበር ዶ/ር ችሮታው አንስተዋል።
ይህ ሁኔታ በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ጭምር ያጋጠመ ውስንነት እንደሆነ በትምህርት ሚኒስቴር ጭምር ግንዛቤ የተወሰደበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ጋር በተያያዘ በልዩ ሁኔታ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ካልተቻ ችግሩ አሳሳቢ መሆኑን ዶ/ር ችሮታው አያይዘው ገልጸዋል።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት አመታት በጤናና በሕግ ትምህርት ቤቶች በተሰጡት የመውጫ ፈተናዎች የላቀ ውጤት ማስመዝገቡን አስታውሰው፤ ዘንድሮም በሁሉም ትምህርት ክፍሎች በተሰጡ የመውጫ ፈተናዎች ይህን ውጤት ለመድገም እንደተቋም ከወራት በፊት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ስራዎች እየተገመገሙ በሰፊው ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ የፈተና ግብረ ኃይሉን ጨምሮ የዞኑና የከተማው አስተዳደር፣ የፀጥታ ዘርፍ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራንና የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች እንዲሁም የአይ.ሲ.ቲ ዳይሬክቶሬት ከሙሉ አባላቱ ጋር ሆነው ከፍተኛ ድጋፍና ርብርብ ማድረጋቸውን የገለፁት ፕሬዝዳንቱ፣ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ በማድረጋቸው ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፈተናቸውን አጠናቀው ሲወጡ ያገኘናቸው ተመራቂ ተማሪዎቹ ቅድስት ደገፉ እና በቃሉ ሽታ በበኩላቸው፤ ፈተናው በጥሩ ሁኔታ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ ዘንድሮ በአገራችን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቃን የመውጫ ፈተና መጀመሩ እንደ ሀገር ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠትና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለውናል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ