የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል በላብራቶሪ ዘርፍ የ"ISO" እውቅናን አገኘ

ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 09/11/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል በቲቢ ምርመራ(Gene xpert) ላብራቶሪ ዘርፍ በISO የጥራት ደረጃ መዳቢ ድርጅት የእውቅና ሰርቴፍኬት ማግኘቱ ተገለጸ።
ዶ/ር ዘርሁን ተስፍዬ፣ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈፃም ተወካይ አንደገለፁት፤ ድርጅቱ በጤናው ዘርፍ በየስራ ክፍሉ ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት ያሟሉትን እውቅና እየሰጠ መምጣቱን አስታውሰው፤ የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጂ ጠቅላላ ሆስፒታል በቲቢ ምርመራ (Gene xpert) ላብራቶሪ ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ መዳቢ ከሆነው ISO እውቅና ማግኘቱን ገልጸዋል።
ይህ እውቅና ድርጅቱ ያስቀመጠውን መስፈርት ማሟላቱን በማየት አዲስ አበባ በተካሄደው 8ኛው ብሔራዊ የጤና ላብራቶሪ ፎረም በቲቢ ምርመራ ዓለምአቀፍ ደረጃ ያሟላን በመሆኑ የተሰጠ እውቅና ነው ሲሉ ይገልፃሉ።
ዶ/ር ዘርሁን አክለው፤ በህክምናውም ሆነ በመማር ማስተማሩ ዘርፍ፤ በወባ ምርመራና በተለያዩ የቤተሙከራ ዘርፎች ይህን የመሰለ ዓለምአቀፍ እውቅና ለማግኝት እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህ ውጤት መገኘት የላብራቶሪ ባለሙያዎች ላበረከቱት አስተዋጽኦ አመስግነው፤ በቀጣይ በተለያዩ ዘርፎች መሰል እውቅና ለማግኘት ተስፋ ሰጭ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።
ዶ/ር እንግዳወርቅ ማሩ፣ በኮሌጁ የህክምናና ስልጠና ዳይሬክተር ተወካይ በበኩላቸው፤ እውቅናው ለላብራቶሪ ዘርፍ የተቀመጠውን መመዘኛ መስፈርት ማሟላቱን በመገምገም በቲቢ ምርመራ (gene xpert) መሰጠቱን ተናግረዋል።
አቶ አስቻለው ገመዴ፣ የላብራቶሪ ክፍል ኃላፊ ተወካይ እንደገለፁት፣ ይህ ውጤት የመጣው እንደ ክፍል በማቀድና በተነሳሽነት በመስራታችን ነው ብለዋል። አክለውም፤ በየወቅቱ የሚሰጡ አስተያየቶችን በመቀበልና በማረም የተጠየቀውን በማሟላት የተገኝ ውጤት እንደሆነ ገልጸዋል።
በቀጣይም በበርካታ ዘርፎች ዓለምአቀፍ እውቅና የሚቀናጁ ስራዎችን ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ አቶ አስቻለው ተናግረዋል።
..................
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ