ዲ.ዩ፦ ሐምሌ 10/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በአገርአቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ያለው "ነገን ዛሬ እንትከል" የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር አካል የሆነ የችግኝ ተከላ በዲላ ዩኒቨርሲቲ እፅዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ከማለዳ ጀምሮ ተከናውኗል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ጊዜያትም በደን ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልፀው፣ በዛሬው እለት ከ17 ሽህ በላይ ችግኞችን በመትከል ላይ ነን ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲው ቡና እና ቀርከሃን ጨምሮ የተለያዩ ዝርያ ያላቸው 532 ሽህ ያህል ችግኞችን ቀድሞውኑ ለመትከል አቅዶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በችግኝ ተከላው የተሳተፉት የዲላ ከተማ ከንቲባና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጂ ጠቅላላ ሆስፒታል ቦርዲ ሰብሳቢ አቶ ተስፋጽዮን ዳካ በበኩላቸው፣ ዩኒቨርሲቲው በእፀዋት አጠባበቅ ዙርያ ያለውን ተነሳሺነት አድንቀው፣ በማዕከሉ በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ፣ ከከተማው አመራር ጋር በጋራ የዛፍ ችግኝ ተከላ ተከናውናል ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የእፀዋት ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ማዕከል ዳይሬክተር ተወካይ ታልሞስ ሴታ (ዶ/ር)፣ ይህ ማዕከል በርካታ እፀዋት ያሉበት ቢሆንም አሁን የተተከለው ችግኝ እንደ ሀገር የደን መመናመንን በእጅጉ ይፈታል ብለዋል። ዋናው መትከል ብቻ ሳይሆን የተተከሉትን በአግባቡ በመንከባከብ ለፍሬ ማብቃት ይገባል ነው ያሉት ዶ/ር ታልሞስ።
በእለቱ በችግኝ ተከላው ሲሳተፉ ያገኘናቸው የዲላ ከተማ ብልጽግና ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ተጠሪ አቶ አብነት አክሊሉ ዛሬ በአንድ ጀምበር 500 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታስቧል፤ የዚያ ዘመቻ አካል የሆነው ይህ የችግኝ ተከላ የጧት መርሃግብር ውጤታማ ነበር ብለዋል።
እርሳቸው አክለውም ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለአረንጓዴ አሻራ ስራ መጠናከር ቁርጠኛ መሆኑ የሚመሰገን ነው ብለዋል። በችግኝ ተከላው የዲላ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራር አካላት፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራር አባላት፣ የየዘርፍ ኃላፊዎች፣ ሰራተኞች ተሳትፈዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ