ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል

ዲ,ዩ፦ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ዲላ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በመጀመሪያ፣ በሁለተኛ እና ሶስተኛ ዲግሪ መርሃ ግብር ያሰለጠናቸውን 1829 ተማሪዎች በዛሬው ዕለት በድምቀት አስመርቋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር )፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ለ2015 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎች፣ ለተመራቂ ወላጆች እንዲሁም ለተማሪዎች ለምረቃ መብቃት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው፤ በተለይም ተመራቂዎች በዘንድሮ ዓመት በልዩ ሁኔታ ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተሰጠውን የመውጫ ፈተና አልፈው የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ለምረቃ መብቃታቸውን አድንቀዋል።
በዚህ ዓመት የምናስመርቃቸው የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው በገቡበት ወቅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተከስቶ የነበረ በመሆኑ በብዙ ወጣ ውረድና መመላለስ ውስጥ አልፈው ለምረቃ መብቃታቸው እንደ ዩኒቨርሲትም ሆነ እንደ ሀገርም የሚያኮራ ተግባር መሆኑንን ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ አያይዘውም በዩኒቨርሲቲው የመውጫ ፈተና ከወሰዱት አጠቃላይ ተማሪዎች ውስጥ ዩኒቨርሲቲያችን ከ72 በመቶ በላይ እንዲያልፉ በማድረጉ ትልቅ ውጤት መሆኑንና ከዚህ የበለጠ ለመስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
አያይዘውም፤ በነበረው የመውጫ ፈተና የጋዜጠኝነት እና ሥነ-ተግባቦት፣ የጌዴኦፋ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ እንዲሁም የኦሮምኛ ቋንቋና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍሎች ያስፈተኟቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ በማሳለፍ በዩኒቨርሲቲው ቀዳሚ ስፍራ መያዛቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በዩኒቨርሲቲው ካሉት ኮሌጆች ውስጥ የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌች ካሳፈተናቸው ተማሪዎች መካከል ከ94 በመቶ በላይ በማሳለፍ ከሁሉም ኮሌጆች አብላጫ ውጤት አምጥቶ ማሳለፍ መቻሉን ገልጸዋል።
ተመራቂዎች ምንም እንኳ ከተቋሙ ተመርቀው ቢወጡም በዩኒቨርሲቲው አልሙናይ በኩል ቤተሰባዊ ግንኙነቱ እንደሚቀጥል የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይ ምሩቃኑ በሚሄዱበት መስክ ሁሉ ዩኒቨርሲቲያቸውንና ሀገራቸውን የሚያኮሩ እንዲሆኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የእለቱ ክብር እንግዳ የከተማ እና መሰረት ልማት ሚኒስትር እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ስብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ ባደረጉት ንግግር፤ ትምህርት የሁሉም ልማቶች መሠረትና የሁሉም ችግር መፍቻ መሳሪያ በመሆኑ፤ መንግስት ከለዉጡ በኃላ የትምህርት ተደራሽነትን ትኩረት በመሰጠት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ዘርፈ ብዙ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ ለዕለቱ ተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክትም "የዛሬ ተመራቂዎች ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋችሁ የተጀመረውን የትምህርት ጥራት መረጋገጫ አንዱ የሆነውን የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና አልፋችሁ ለዚህ ሰለበቃችሁ እንኳ ደስ አላችሁ" ብለዋል።
የዩኒቨርሲቲው የሬጅስትራልና አልሙናይ ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ይልማ በዕለቱ በድህረ ምረቃ መርሃግብር በሶስተኛ ድግሪ ፕሮግራም ሁለት ወንድ ምሩቃን ፣ በሁለተኛ ዲግሪ 82 ወንድ እና 18 ሴት በድምሩ 100፣ በመደበኛው መርሃግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 1188 ወንድ እና 402 ሴት በድምሩ 1590፣ በስነ-ማስተማር ዘዴ በከፍተኛ ዲፕሎማ (HDP) 118 ወንድ እና 19 ሴት በድምሩ 137፣ በአጠቃላይ 1390 ወንድ እና 439 ሴት በድምሩ 1829 ተማሪዎች ለምረቃ መብቃታቸውን አብስረዋል።
በዕለቱ የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል ከቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ከኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ምሩቅ የሆነው መላኩ ልንገረው አጠቃላይ ውጤት 3.95 በማምጣት ዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል።
የማዕረግ ተመራቂው መላኩ ልንገረው በዩኒቨርሲቲው የነበረው የትምህርት ቆይታ በእንዲህ ባለ አስደሳች ውጤት ማጠናቀቅ መቻሉ እንዳስደሰተው ገልጾልናል። ለዚህም ውጤት መመዝገብ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ላበረከቱለት መምህራኖቹ እና ቤተሰቦቹ ምስጋናውን ገልጿል።
በበዓሉ ላይ የእለቱ የክብር እንግዳ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር እና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደር እና የዲላ ከተማ አስተዳደር አመራር አካላት፣ የሴኔት አባላት፣ በተለያየ እርከን የሚገኙ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና መምህራን፣ አባገዳዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል ልዩ ልዩ ጥዑመ ዜማዎችን በማቅረብ ዝግጅቱን አድምቆታል።
ተመራቂዎቻችን በድጋሜ እንኳን ደስ አላችሁ!
ዲላ ዩኒቨርስቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ