ዲ,ዩ፦ ሐምሌ 13/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማና መሰረት ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትርና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በተገኙበት፤ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ነባር ህንፃዎች የሁለተኛ ዙር እድሳት የተጠናቀቁ እንዲሁም በሐሴዴላ ግቢ ዘመናዊ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ህንጻዎች ተመርቀዋል።
ኢንጂነር በፍቃዱ መኩሪያ፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ፤ በሁለቱም ጊቢዎች የተሰሩ የግንባታ ስራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ኢንጂነር በፍቃዱ፤ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጠቅላላ ሆስፒታል ስር በሁለተኛ ዙር እድሳት ተደርጎላቸው በዛሬው እለት የተመረቁት የአገልግሎት መስጫ ክፍሎች፤ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ እንዲሁም በመማር ማስተማር መካከል ሆነን፤ አገልግሎቱም ትምህርቱም ሳይቋረጥ ጎን ለጎን እድሳቱን በማካሄድ የተሻለ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት ደረጃ አድርሰን ለምርቃ አብቅተናል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢንጂነሩ እንደገለጹት፤ በተለይ በሐሴዴላ ተገንብተው በዛሬው ዕለት የተመረቁት ሁለቱ የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽና የምግብ ማብሰያ ህንፃዎችን ጨምሮ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የሆኑ የመሰረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ባለፉት ሶስት አመታት በጊቢው የመማሪያ ህንፃዎችን ጨምሮ፣ የተማሪዎች ማደሪያ (ዶርሚተሪዎች) እንዲሁም ዛሬ የተመረቀውን የተማሪዎች የመመገቢያ አዳራሽ (ካፍቴሪያ) በአጠቃላ 1.8 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ እንደተደረገበት አንስተው፤ በዚህም ለአካባቢው ማህበረሰብ የስራ እድል እንደፈጠረም ጭምር አስረድተዋል።
ኢንጂነር በፍቃዱ አክለውም፤ በዛሬው ዕለት የተመረቁት የተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ህንጻዎች፤ በአንድ ጊዜ ከአንድ ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን ማስተናገድ የሚችሉ እንደሆኑም ገልጸዋል።
ክብርት ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ሚኒስትርና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፤ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት፤ የተሰራው ስራ ከተቋም ባለፈ የአገር ሃብት መሆኑንም ጠቅሰዋል። እርሳቸው አክለውም ብዙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ያላቸውን ሃብትና ፀጋ መንከባከብና አካባቢውን በሚገልጽ መልኩ አረንጓዴአማነትን እንደተቋምም ማስጠበቅ እንደሚገባ አንስተዋል።
ክብርት ሚኒስትሯ አያይዘውም፤ እንደ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የራሳቸውን ገቢ ማመንጨት እንዳለባቸው ከተቀመጠው አቅጣጫ ጋር በሚጣጣም መልኩ ስራዎች የተቃኙና የራስን ገቢ በሚያጎለብቱ መልኩ እንዲሆኑ አሳስበዋል።
የተሰሩ ስራዎች አበረታችና መልካም እንደሆኑ ገልጸው፣ ለዚህ ስኬት ለታተሩ አካላት ክብርት ሚኒስትሯ ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል።
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው፤ እንደ አገር የግንባታ ዘርፉ ችግር በተጋረጠበት ወቅት ህንፃዎቹን በትጋት ሰርተው ለዚህ ላበቁ አካላት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ የሐሴዴላ ግቢ በአገር ደረጃ የግንባታ ጥራት ካላቸው ግቢዎች አንዱ እንደሚሆን ገልጸው፤ የተማሪ ማደሪያ ህንፃዎቹ (ዶርሚተሪዎች) ዘመናዊና ጥራታቸውን የጠበቁ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንን ቦታ ተቋሙ እንዲያለማበት በቅንነት ፈቅዶ ለሰጠን ለአካባቢው ማህበረሰብ ከልብ የሆነ ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
በእለቱም የዲላ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ አባ ገዳዎች፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴነት አባላት፣ የዩኒቨርሲቲው አመራር አባላት፣ የጌዴኦ ዞን አስተዳደርና የዲላ ከተማ አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ