ዲ.ዩ፡- ሐምሌ 17/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በመጀመሪያው ዙር (ማህበራዊ ሳይንስ) የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከትላንት ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ እየገቡ ነው። ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱም ዙር 17 ሽህ አካባቢ ተማሪዎች ተቀብሎ ይፈትናል።
የመጀመሪያ ዙር ተፈታኝ ተማሪዎቹ ዛሬ ተጠቃለው የሚገቡ ሲሆን የቅድመ ፈተና ገለፃ (Orientation) ነገ ይሰጣል።
አስናቀ ሙሉዬ (ዶ/ር) በዲላ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲሰጥ ባለፈው አመት ጀምሮ የተተገበረ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ ለመስጠት ዲላ ዩኒቨርሲቲም ዝግጅት አጠናቆ ከትላንት ጀምሮ ተማሪዎችን እየተቀበለ ነው ብለዋል።
ፈተናውን በስኬት ለማስኬድ አስፈላጊውን ግብአቶች በሟሟላት እንዲሁም በቂ የሰው ሃይል በመደብ፣ ከአከባቢው አስተዳደርና የሚመለከታቸው የፀጥታ አካላት በማቀናጀት ስራው ተጠናቆ ተፈታኝ ተማሪዎችን ከትላንት ጀምሮ ወደ ዩኒቨርሲቲው እየገቡ ነው። የመጀመሪያ ዙር ማለትም የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ረቡዕ፣ ሐምሌ 19/2015 ዓ.ም ፈተናውን እንደሚጀምሩ የተያዘው መርሃግብር ያመላክታል።
እንደ ዶ/ር አስናቀ ገለጻ እርሳቸው በሚመሩት የአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዘርፍ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ዋና ግቢ፣ ኦዳያአ እና ሐሴዴላ ግቢዎች ለሚሰጠው ፈተና በግቢዎቹ ለተመደቡ ተማሪዎች በቂ የመኝታ ቦታ፣ የምግብ አቅርቦትና መመገቢያ አዳራሾች፣ የህክምና አገልግሎት፣ የመፈተኛ ክፍሎች፣ የመዝናኛ አዳራሾች እና ካፍቴሪያዎች ተዘጋጅተዋል፡፡
ፈተናውን ለማስፈፀም ለመጡ ከአራት መቶ በላይ ፈታኝ መምህራን፣ አስተባባሪዎች እና ሀላፊዎች በቆይታቸው የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ የማስቻል ስራ ከዲላ ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ቀደም ብሎ ጀምሮ እየተሰራ ነው ብለዋል ዶ/ር አስናቀ።
በትምህርት ሚኒስቴር መርሃ-ግብር መሠረት ከሐምሌ 19-21/2015 ዓ.ም ድረስ በሚሰጠው የማህበራዊ ሳይንስ ፈተና ተፈታኞችን መልካም እድል እንዲገጥማቸው ዶ/ር አስናቀ ተመኝተዋል፡፡
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ