ዲ.ዩ፡- ሐምሌ 18/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ):- የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት ከተጀመረ ሁለተኛ ዙር በሆነው የዘንድሮው ፈተና መርሃግብር በዲላ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ የመጀመሪያ ዙር ማለትም የማሕበራዊ ሳይንስ ተፈታኝ ተማሪዎች ስለ ፈተና አሰጣጥና በግቢ ውስጥ ስለሚኖራቸው ቆይታ ገለጻ (Orientation) ተደርጎላቸዋል፡፡
ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት በገላጻው ወቅት እንደተናገሩት፤ ከደ/ብ/ብ/ሕ/ ክልል ጌዴኦ ዞን፣ ከአጎራባች የሲዳማ ክልል አካባቢዎች፣ እንዲሁም ከሶማሌ ክልል ተመድበው ወደ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለመጡ ተፈታኝ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ የ12 ዓመት የልፋት ውጤታችሁ የሆነውን የትምህርት ጉዟችሁን በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ፤ ፈተናውን በተረጋጋ መንፈስ ወስዳችሁ፣ የልፋታችሁን ዋጋ እንድታገኙ የዩኒቨርሲቲው አመራርና ማህበረሰብ በሙሉ 24 ሰዓት ባለመታከት ከጎናችሁ በመሆን አስፈላጊውን አገልግሎት ይሰጣችኋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የምትወስዱት ፈተና የተማራችሁትና የምታውቁት በመሆኑ በጥንቃቄና በራስ መተማመን መንፈስ ሰርታችሁ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ፤ በቀጣይ አመት ዲላ ዩኒቨርሲቲን መርጣችሁ እንደምትቀላቀሉን ተስፋ አለኝ ብለዋል ፕሬዝዳንቱ፡፡
ከትምህርት ሚኒስቴር በዲላ ዩኒቨርሲቲ ፈተና ማዕከል ኃላፊ ሁነው ከተመደቡት አንዱ የሆኑት አቶ እሱባለው ወንድም በበኩላቸው፤ በታሪክ አጋጣሚ ለሁለተኛ ጊዜ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚሰጠው ብሔራዊ ፈተና አካል ሆናችሁ ይህንን ፈተና የምትወስዱ ሁሉ፤ ፈተና በባህሪው ትኩረት እና ጥንቃቄ የሚፈልግ እንዲሁም አብዝቶ መጨነቅ የማይፈልግ መሆኑን ተረድታችሁ ፈተናችሁን በተረጋጋ መንፈስ እንድትፈተኑ ሲሉ ተማሪዎችን አሳስበዋል፡፡
አቶ እሱባለው አክለውም፤ በፈተና ወቅት አስፈላጊ የሆኑ መለያ ቁጥር፣ የፈተና ቁጥር፣ የትምህርት ዓይነት መለያ ቁጥር (ኮድ) እና ሌሎች መረጃዎችን በጥንቃቄ መሙላት እንዳለባቸው ተማሪዎቹን አደራ ብለዋል፡፡ ተማሪዎች ሰዓታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙና ፈተናው ተጀምሮ 30 ደቂቃ ካለፈ በኋላ መግባት ፈጽሞ እንደማይቻል፣ ፈተና ከተጀመረ 45 ደቂቃ በፊት ከመፈተኛ ክፍል መውጣት እንደማይቻል፣ ፈተናው ለመጠናቀቅ 15 ደቂቃ ሲቀር ለፈተናው የተሰጠው ሰዓት ሣይጠናቀቅ መውጣት እንደማይቻልም አሳስቀዋል። እርሳቸው አክለውም የፈተናው ሰዓት ሳያልቅ የፈተና ወረቀት (Sheet) ይዞ መውጣት እንደማይቻል ለተማሪዎች አስገንዝበዋል፡፡
አስናቀ ሙሉዬ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ በበኩላቸው፤ ተፈታኝ ተማሪዎች በግቢ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የሚያስፈልጋቸው አገልግሎት በበቂ ሁኔታ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ በተቋሙ ውስጥ የሚገለገሉባቸውን ንብረቶች በንጽህናና በአግባቡ እንዲይዙ አሳስበዋል።
በፈተና ወቅት ከሚኖረው የሰአት መጣበብ የተነሳ መስተጓጎል እንዳንፈጠር ወደ መመገቢያ አዳራሽ ሲመጡ በአግባቡ ሰልፍ ይዘው መስተናገድ እንዲችሉ፣ እንዲሁም የህመም እና ስነ-ልቦናዊ የመረበሽ ስሜት ሲያጋጥማቸው በዩኒቨርሲቲው በሁሉም የመፈተኛ ግቢዎች የጤና ባለሙያ ተመድቦላቸው ለዚሁ አላማ የተዘጋጁ የህክምና ማዕከላት ስላሉ ወደ እነዚህ ማዕከላት በመሄድ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚችሉ አሳውቀዋል፡፡
ኮማንደር አማረ ገራው፣ በዲላ ዩኒቨርሲቲ የፈተና ማዕከል የፌዴራል ፖሊስ አስተባባሪ፤ ከጸጥታና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ለተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
ኮማንደሩ በመልዕክታቸው ለጋራ ደህንነት ሲባል ተማሪዎች የተሰጣቸውን ደንብና መመሪያ አክብረው እንዲቀሳቀሱ ጠቁመው፤ በቡድን ሆኖ ማነኛውንም ፀጥታ የሚያውክ ድምፅና እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ከግቢ ለመውጣት፣ በአጥር በኩል ከውጭ የተከለከሉ እቃዎችን ለመቀበል መሞከር እንዲሁም ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችን ይዞ መገኘት ወንጀል መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎች የመጡለትን አላማ በስኬት ለማከናወን ይረዳ ዘንድ ሰዓታቸውን አክብረው መገኘት ባለባቸው ቦታና ሰአት በመገኘትና ለፍተሻ ተባባሪ በመሆን ሰላማዊ የፈተና ጊዜ እንዲሆን እንዲተባበሩ ኮማንደር አማረ አሳስበዋል፡፡
የቅድመ ፈተና የጋራ ገለፃው በተመሳሳይ ሰአት በቀድሞው ዋና ግቢ፣ ኦዳያአ ግቢና ሐሴዴላ ግቢ በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ በትምህርት ሚኒስቴር ተወካዮች እና በፌዴራል ፖሊስ አመራሮች ተሰጥቷል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ ነገ በሚጀምረው የማህበራዊ ሳይንስ መስክ ፈተና ከ14 ሽህ በላይ ተማሪዎችን እንደሚፈትን መዘገባችን ይታወሳል።
#ምስል፦ ከኦዳያአ ግቢ፣ የቀድሞው ዋና ግቢ እና ሐሴዴላ ግቢ
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ