የ12ኛ ክፍል ፈተና አስፈፃሚዎች በጌዴኦ ዞን የሚገኙ የትክል ድንጋይ መካነ-ቅርሶችን ጎበኙ

ዲ.ዩ፤ ሐምሌ 23/2015 ዓ/ም (ህ.ዓ.ግ)፦ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ለ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ተመድበው የፈተና ሂደቱን ሲያስፈጽሙ የቆዩ መምህራን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቱሪስት መስህብ የሆኑትን የጨልባ ቱቲቲ ታሪካዊ ትክል ድንጋዮች ጎብኝተዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ ከጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር፤ የ12ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና የመጀመሪያ ዙር የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ፈተና መጠናቀቁን ተከትሎ የጉብኝት መርሃግብር አዘጋጅተዋል።
አቶ ተስፋዬ በደቻ፣ የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ተወካይ፤ በዞኑ የተለያዩ የቱሪዝም መስህቦች መኖራቸውን አስረድተዋል። በምስራቅ አፍሪካ ካሉት 10 ሺህ ትክል ድንጋዮች መካከል በጌዴኦ ዞን በስድስት ቦታዎች ብቻ ከ6ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች ይገኛሉ ብለዋል አቶ ተስፋዬ። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ እንግዶቹ በጎበኙት ጨልባ ቱቲቲ ብቻ ከ1600 በላይ ትክል ድንጋዮች እንደሚገኙ ለጎብኝዎች ገልጸዋል።
አቶ ተስፋዬ አክለውም፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም በሆነው ዩኔስኮ (UNESCO) በጥምር እርሻ፣ ትክል ድንጋይ እና ሌሎች ቅርሶችን ለማስመዝገብ ጥረት እተደረገ መሆኑንና በጉብኝቱ የተሳተፉ መምህራን በምርምር እና በማስተዋወቅ ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አካፍለዋል።
ሀሳባቸውን ያጋሩን በጉብኝት መርሃግብሩ ከተሳተፉት መካከል አቶ ፍቃዱ አበበ እና መምህርት ሰብለ ብርሃኑ፤ በቆይታቸው የዲላ ህዝብ ሰላም ወዳድና እንግዳ አክባሪ እንደሆነ መገንዘባቸውን ጠቅሰው፤ ዲላ ዩኒቨርሲቲ ላዘጋጀላቸው ጉብኝት እንዲሁም ላደረገላቸው መልካም መስተንግዶ ምስጋናቸውን አቅርቧል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ