ዲ.ዩ፤ ሐምሌ 28/2015 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፤ በአገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ በሁለት ዙሮች ሲሰጥ የቆየው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ዛሬ ተጠናቋል፡፡ በዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለት ዙር ሲሰጥ የቆየው ብሄራዊ ፈተና መጠናቀቁን አስመልክቶ፤ ችሮታው አየለ (ዶ/ር)፣ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት እንዲሁም ወ/ሮ ፈንቱ ኤልዶ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ እና በፈተናው የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጉድኝት ማዕከል ኃላፊ በጋራ መገለጫ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ችሮታው አየለ በመገለጫቸው፤ ለ15 ቀናት በሁለት ዙር ሲሰጥ የቆየው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል። ለዚህም ባለፈው አመት ፈተና በሚሰጥበት ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን እንደ ተቋም አስቀድሞ ከግንዛቤ በማስገባት እና ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ከፀጥታ አካላት፣ ከፈተናዎች ኤጀንሲ፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች፣ ከጉድኝት ኃላፊዎች፣ ቺፎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ፈታኞችና ሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት በመሰራቱ አመርቂ ውጤት ማምጣት መቻሉን ተናግረዋል።
ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በተገናኘ ሁሉም የተጣለባቸውን አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት ሲሰሩ መቆየታቸው ገልጸው፤ ነገር ግን በሐሴዴላ ግቢ በጥበቃ ሥራ ከነበሩ ሁለት አባላት ያልተገባ ባህሪ በማሳየታቸው በአፋጣኝ ከስራቸው ተነስተው ወደ ፌዴራል መንግስት እንዲሄዱ ከመደረጉ ውጪ በከፍተኛ ትጋት ሰርተው ተቋሙ ፈተናውን በሰላም እንዲያጠናቅቅ ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
እንዲሁም ከተማሪዎች ጋር በተገናኘ ዶ/ር ችሮታው ሲያብራሩ፤ በቀድሞው ዋና ግቢ የማህበራዊ ሳይንስ ዘርፍ የጂኦግራፊ ትምህርት ፈተና በሚሰጥበት ወቅት በአንድ ህንጻ ላይ አንድ ተማሪ በወንበር መስኮት በመስበሩ ምክንያት ሕንጻው ላይ በነበሩ ተማሪዎች የተወሰነ መደናገጥ ተፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፤ በተወሰደ የማረጋጋት እርምጃ ተማሪዎች ፈተናቸውን ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሰዓቱ ከግቢው ውጪ ሲሰራጩ የነበሩ አሉባለታዎች፣ የፈተና ሂደቱን ለመረበሽ የተደረጉ ሙከራዎች እንደነበሩ ጠቁመው፤ ነገር ግን ፈተናውን በስኬት አጠናቀናል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
ዶ/ር ችሮታው አክለውም፤ ብሔራዊ ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ፤ የፈተና ግብረ ሀይሉን ጨምሮ የፀጥታ ዘርፍ፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራር፣ የአስተዳደር ዘርፍ ሰራተኞች እንዲሁም የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ከሙሉ አባላቱ ጋር ሆነው ተማሪዎችን በመቀበል፣ ለተማሪዎች ሰዓት በማሳወቅ፣ ቅስቀሳዎችን በማድረግና በመሸኘት ጭምር ርብርብ በማድረጋቸው ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋናቸው አቅርበዋል።
ወ/ሮ ፈንቱ ኤልዶ፣ በትምህርት ሚኒስቴር የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ እና በሀገር አቀፍ ፈተና የዲላ ዩኒቨርሲቲ ጉድኝት ማዕከል ኃላፊ በበኩላቸው፤ የፈተናው ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ እንደ ተቋም ሆነ እንደ ፈተና አስፈጻሚ ከጅማሮ አንስቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ተናቦ በመስራት ተማሪዎችን ያለምንም የዲሲፒሊን ችግር ፈተና ማጠናቀቅ መቻሉን ተናግረዋል።
በፈተና ወቅት ከጤና ጋር ተያይዞ አልፎ አልፎ የተወሰኑ ችግሮች እና ልጅ የመውለድ ክስተቶች የነበሩ ቢሆንም፤ ዩኒቨርሲቲው በሁሉም ግቢዎች ላይ በቂ አምቡላንስና የጤና ባለሙያዎች አዘጋጅቶ ስለነበር የተለየ ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ለችግሮች መፍትሔ እየተሰጠ ፈተናው በሁለቱም ዙር በሰላም መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ከአቀባበል ጀምሮ ለተደገላቸው መልካም መስተንግዶ ምስጋናቸውን አቅርበው፤ በፈተናው ወቅት ማህበረሰቡ ኩረጃን የሚጠየፍ ጨዋ ልጆችን ለፈተናው በመላኩ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል።
የጸጥታ አካላቱም፤ ፈተና ከደረሰበት ሰዓት አንስቶ ፈተናው እስኪጠናቀቅ ድረስ የአካባቢውን ደህንነት ለ24 ሰዓት በንቃት በመጠበቅ ፈተናው በስኬት እንዲጠናቀቅ ለተጫወቱት ትልቅ ሚና ያላቸውን ምስጋና ገልጸዋል።
በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ በዚህኛው ዙር ፈተናቸውን አጠናቀው ሲወጡ ያነጋገረናቸው ተፈታኞች ተማሪ ዳግማዊት ወንድሙ እና ተማሪ በረከት ማርቆስ በበኩላቸው፤ ፈተናው በሰላም መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በዩኒቨርሲቲው ከመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል እና ለነበራቸው ቆይታ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ በሁለቱም ዙሮች በጥቅሉ ከአጎራባች ሲዳማ ክልል፣ ከጌዴኦ ዞንና በመጀመሪያው ዙር ደግሞ ከሶማሌ ክልል ጭምር የተመደቡለትን ከ16 ሽህ በላይ ተማሪዎች ተቀብሎ ፈትኗል። ዛሬ ፈተናቸውን ያጠናቀቁትን ተማሪዎችም ወደየአካባቢያቸው ሸኝቷል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ