የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ወስኗል

ዲ.ዩ፦ መስከረም 06/2016 ዓ.ም (ህ.ዓ.ግ)፤ የተባበሩት መንግስታት የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በጌዴኦ ዞን የሚገኘው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በመንግስታቱ የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ውስኗል።
ኮሚቴው ዛሬ ባካሄደው 45ኛ ጉባኤው የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ያለውን ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ፋይዳ ታሳቢ በማድረግ በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ መወሰኑን ነው ያስታወቀው።
በጉባኤው ከኢትዮጵያ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ እና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር) ስለ ጌዴኦ ማኅበረሰብ አኗኗር እና ባህላዊ መልክዓ ምድሩ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ መስጠታቸውን ኢቢሲ ዘግቧል።
መልክዓ ምድሩ በምስራቅ አፍሪካ ረዥም እድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት የትክል ድንጋይ መካነ ቅርስ እንዳለው፣ በዚህም በመልከዓ ምድሩ ከስድስት ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች እንደሚገኙ፣ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች እንዲሁም ለውጭና ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች ቀልብ የሚስብ ገጽታን የተላበሰ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባሻገርም መልክዓ ምድሩ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲሸጋገር የቆየ ጥብቅ ደን የያዘ ሲሆን፤ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ በጥብቅ አያያዝ ከቆየው የደን ሃብት ጋር የሚጣጣም የጥምር ግብርናም የሚካሄድበት መሆኑ ልዩ ያደርገዋልም ነው የተባለው።
የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ረዝም ጊዜ የጥናትና ምርምር፣ የሰነድ ማደራጀት ስራዎች ሲሰሩ የነበረ ሲሆን ዲላ ዩኒቨርሲቲም በስራው የላቀ አበርክቶ ሲያደርግ ቆይቷል።
የመልከዓ ምድሩ መመዝገብ ለቅርሱ ዘላቂ እንክብካቤ እንዲያገኝ ከማስቻል ባለፈ ትልቅ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን ያስችለዋል ተብሎም ይጠበቃል። ዲላ ዩኒቨርሲቲም ለጌዴኦ ማህበረሰብ፣ በዚህ ስራ ለተሳተፉ ሁሉና ለኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ እያለ መልካም ምኞቱን ይገልፃል።
ዲላ ዩኒቨርሲቲ
የአረንጓዴው ምድር ዩኒቨርሲቲ