ዲላ ዩኒቨርሲቲ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ እየሠራ ይገኛል

ዲዩ፤ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም (ሕ.ግ) ዲላ ዩኒቨርሲቲ ያረጁ ቡናዎችን በመጎንደል፣በመንቀልና በምትካቸው አዳዲስ በምርምር ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞችን በማፍላትና ለአርሶ አደሩ የማዳረስ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ የምር/ቴ/ሽ/ም/ፕ ዶ/ር ፍሬ ሕይወት እንዳለ ገልጸዋል፡፡
የቡና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለመቀየር በዲላ ዙሪያና በወናጎ ወረዳዎች በተመረጡ 50 አርሶ አደር ማሳዎች የጉንደላና አዳዲስ ምርታማ ችግኞችን የመትከል ሥራዎችንም በቅርበት ክትትልና ድጋፍ እያደረገ እንደሆነ በዛሬው ዕለትበዲላ ዙሪያ ወረዳ በሳኮአ ቀበሌ በተረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች ማሳ በተካሄደው የተፋሰስ ልማት ንቅናቄ ላይ ተገኝተው ተናግረዋል፡፡
የቡና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ዓለሙ ደሳ በበኩላቸው ለተመረጡ ሞዴል አርሶ አደሮች ዘርፈ ብዙ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው በኩል እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡የእርሻ መገልግያ መሣሪያዎች ጨምሮ የተጎነደለውና አዲሱ የቡና ችግኝ እስኪደርስ ተጓዳኝ የሆኑ እንደ ቦሎቄና መሰል ሰብሎችን እያመረቱ ኑሯቸውን እንዲደግፉ የአጭርና የረጅም ጊዜ ሥልጠናና ድጋፍም እንደሚደረግ አስታወቀዋል፡፡
አንድ ሄክታር ማሳቸውን ለአዲሱ ምርትና ጉንደላ ያዘጋጁት አርሶ አደር ግዛው ቦረና ከዚህ ቀደም ቡናው በማርጀቱ ከአንድ ሄክታር ማሳ ከሶስት ኩንታል ያልበለጠ ጊዜ ያገኙ እንደነበረና አሁን ይህን ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡