ዲላ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አስመረቀ

ዲላ ዩኒቨርሲቲ ለማህበረሰብ አገልግሎት ፋይዳ ያላቸውን ሦስት ፕሮጀክቶችን አስመረቀ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትን ታሳቢ በማድረግ ካከናወናቸው ፕሮጀክቶች መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ተኮር የሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ.ኤም 89.0፣ የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማዕከልና የወተት ላሞች እርባታና ቴክኖሎጂ ጣቢያ ይገኙበታል፡፡ በምርቃት ሥነ-ስርዓቱ ተገኝነተው ፕሮጀክቶችን የመረቁት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን የማህበረሰብ ሬዲዮው ለማህበረሰቡ ከማስተማርና ግንዛቤን ከመፍጠር አንጻር ፋይዳው ከፍተኛ በመሆኑ ማህበረሰቡ የሚያዳምጥ ብቻ ሳይሆን የሚሳተፍበት እንዲሆን መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አክለውም የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማዕከልም ሆነ የወተት ላሞች እርባታና ቴክኖሎጂ ጣቢያው ለህብረተሰቡ ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው በማት ገልጸዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ ሽፈራው ቦጋለ በበኩላቸው የሬዲዮ ጣቢያ መከፈቱ የአካበቢው ማህበረሰብ መረጃ ለማግኘት ያለውን አማራጭ የሚያሰፋና በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ምክክር ለማድረግ ሰፊ ዕድል የሚሰጥ ነው፤ብለዋል፡፡ የዲላ ዩኒቨርሲት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እነዚህ ፕሮጀክቶች ዋና ዓላማቸው ማህበረሰቡን በሁሉም ረገድ ለማገዝና የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ ለማስቻል የሚያግዙ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ለሦስቱም ፕሮጀክቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ዩኒቨርሲቲው ወጪ ማድረጉን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ከጊዜ ወደ ጊዜ ተደራሽነቱንም ሆነ ጥራቱን ከፍ ባለደረጃ እያሳደገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ፡፡