የዲላ ዩኒቨርሲቲ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ማዕከል ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ልዩ ስልጠና ሰጠ፡፡

ዲ/ዩ 19/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) አካል ጉዳተኝነት ማንኛውንም ስራ መስራት የሚያግድ አለመሆኑን የተናገሩት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ዳይሬክተር ዶ/ር አባቡ ተሾመ አንድ ሰው አካል ጉዳተኛ የሚባለው አንድ የአካል ስሜት ሲያጣ በመሆኑ ይህ የአካል ስሜት ማጣት በህብረተሰብ የሚያሰጠው ስም በየቦታው የተለያየ እንደሆነ አውስተው አላስፈላጊ ስሞችን በማውጣት የአካል ጉዳተኛውን ሞራልም ሆነ ስሜት መንካት አስፈላጊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ያለው ሁኔታ ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ያወሱት ዶ/ር አባቡ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች በተቋሙ ባሉ መሰረተ ልማቶችና ተቋሙ የሚያቀርባቸውን ግብዓቶች በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ጠንክረው መስራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የጋይዳንስና ካውንስሊንግ መምህር የሆኑት ድንቁ በጀጎ በበኩላቸው ስለ ተቋሙ በሰፊው ገለጻ ያደረጉ ሲሆን በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ለመማር ማስተማር አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር ያስችል ዘንድ በአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና በሰራተኞች መካከል ሊኖር የሚገባውን መስተጋብር ግልጽ ያደረጉ ሲሆን ስነ-ልቦናዊና የተለያዩ ተገቢ እገዛዎችን ተማሪዎቹ በሚያገኙባቸው መንገዶች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በስልጠናው የተሳተፉ ያነጋገርናቸው ተማሪዎች ተማሪ ግርማ ብልቻና ተማሪ ጥጋቡ ብርሃኑ በስልጠናው በመሳተፋቸው ደስተኞች እንደሆኑና ጥሩ ግንዛቤም ማግኘታቸውን ገልፀው ተቋሙም ሆነ የልዩ ፍላጎት ትምህርት ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ ልንጠቀምባቸው በሚገቡ አዎንታዊ ቃላት እና ማስወገድ በሚገባን አሉታዊ ቃላት ዙሪያም ሰፊ ገለጻ የተደረገ ሲሆን በስልጠናው አዲስ ገቢ የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች፣ የተለያዩ ትምህርት ክፍል ኃላፊዎችና ለአገልግሎት አሰጣጥ ቅርበት ያላቸው የስራ ክፍል ተወካዮች መካፈላቸውን ለማወቅ ችለናል፡፡