የዲላ ዩኒቨርሲቲ በኮቪዲ 19 መከላከልና መቆጣጠር ባሳየው አፈፃፀም ከክልል ጤና ቢሮ የዋንጫና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጠው::

ዲዩ ሐምሌ 23/2013(ህ.ግ) በአለም ደረጃ የኮቪዲ 19 የመከላከሉና የመቆጣጠሩ ስራ ሲሰራ ሀገራችንም ይህን አስከፊ ወረርሽኝ ለመከላከል የሰራችው ስራ ከፍተኛ ነበር ያሉን የዲላ ዩኒቨርሲቲ ኘሬዝዳንት ዶ/ር ችሮታው አየለ እንደ ተቋምም ዩኒቨርሲቲያችን ከኬንያ በኩል ወደ ሀገራችን ይገቡ የነበሩትን ዜጎች የኳራንቲን አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ የኦክስጂን ፕላንት እስከመትከል ድረስ ሰፋፊ ስራዎች ሲሠሩ የቆዩ እንደነበር አውስተው እንደ ሀገር በነበረው አቅጣጫ ተቋማችን የመማር ማሰተማሩን ሥራ አቁሞ ሙሉ ትኩረቱን ወረርሽኑን በመከላከልና መቆጣጠር ላይ በማድረግ ከፍተኛ ድጋፍ እየሰጠ እንደነበር ተናግረዋል::
ይህ ስራችን ታይቶና ተመዝኖ የተሰጠን እውቅና ነገ ለምንሰራው ስራ ትልቅ አሰተዋፅዖ አለው ያሉን ዶ/ር ችሮታው የዚህ ሽልማት ባለቤቶች መላው የተቋማችን ሰራተኞች በመሆናቸው እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል::
በቀጣይ በተመደብንበት ዘርፍ በርትተን በመስራት የተሻለ ውጤት ማምጣት ይጠበቅብናል ያሉት የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፌራል ሆስፒታልና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ም/ኘሬዝዳንት ዶ/ር ሰላም አየለ የተሰጠን ዋንጫና የምስክር ወረቀት እየሰራን ላለነውና በቀጣይ ላቀድናቸው ስራዎች ከፍተኛ መነሳሳትን ይፈጥራሉ ብለው የክልል ጤና ቢሮም ስራችንን አይቶ ለሰጠን እውቅና ትልቅ አክብሮት አለኝ ብለዋል::
ዶ/ር ዘርሁን ተስፋዬ የህክምናና ተግባር ሥልጠና ዋና ዳይሬክተርና የኮቪዲ 19 አስተባባሪ በበኩላቸው ይህ ወረርሽኝ በተቋማችን ሆነ በዞኑና በአካባቢው ምልክቱ መታየት ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልፀው የጤና ባለሙያውና የድጋፍ ሰራተኛው ያሳየውን ጥምረትና ቁርጠኝነት አድንቀው በቀጣይነትም የዚህ አይነቱ ተነሳሽነት ልቀጥል ይገባል ብለዋል::
.......
እንኳን ደስ አላችሁ÷ እንኳን ደስ አለን!