የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ለሳንባ ነቀርሳ የሚያገለግል ግብዓት (reagent) ለጤና ተቋማት ማሰራጨት ጀመረ፡፡

ዲ.ዩ ሐምሌ 28/11/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) የጤና ተቋማት የመጀመሪያ ስራቸውም ሆነ ዓላማቸው በሽታን መከላከል ላይ ያተኮረ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር ዘሪሁን ተስፋዬ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምናና ተግባር ስልጠና ዋና ዳይሬክተር ዛሬ የሚታደለው ለሳንባ ነቀርሳ የሚያገለግለው ግብዓት (reagent) ከዚህ በፊት በከፍተኛ ወጪና መጉላላት ከክልል ጤና ቢሮ ይመጣ እንደነበር ተናግረው ይህን አሰራር የክልሉ ጤና ቢሮ ቀይሮት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል እንዲቀርብ መደረጉ በዞኑ ያሉትን የጤና ተቋማት ከአላስፈላጊ እንግልትና ወጪ ያስቀረ ነው ብለውናል፡፡
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል የህክምና አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ዶ/ር በረከት ብዙነህ በበኩላቸው ግብዓቱ ከክልል የሚመጣውን አሰራር ለማስቀረት 5 የጤና ባለሙያዎች ተመድበው እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀው ግብዓቱን በዞናችን ላሉት 46 የጤና ተቋማት ስርጭት መጀመሩን ተናግረው በቀጣይ የወባን መመርመሪያ ለማዘጋጀት ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ግብዓቱ የሚተንና በጥንቃቄ ካልተያዘ ለጤና አደገኛ በመሆኑ የጤና ባለሙያዎች ትልቅ ትኩረት ሰጥተው በጥንቃቄ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ አስቻለው ገመዴ የሪፈራል ሆስፒታል የላብራቶሪ ክፍል ኃላፊ በበኩላቸው አሁን ላይ እየተመረተ ያሉት ZN እና FM የሚሰኙ ግብዓቶች እንደሆኑ ተናግረው እነኚህ ግብዓቶች በኛው አቅምና በኛው ተቋም መዘጋጀታቸውን ሪፈራል ሆስፒታሉ ለቀጣይ በርካታ ስራዎችን መስራት እንደሚችል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በወቅቱ ይህንን ግብዓት ሊረከቡ የመጡት የዞኑ ጤና መምሪያ ባለሙያ የሆኑት አቶ መክተው በለጠ ይህን ግብዓት ከክልል ስናመጣ ከፍተኛ ችግር ይገጥመን እንደነበርና ግብዓቱ በትነትም ሆነ በፀሐይ ይበላሽ እንደነበረ ገልፀው ይህን አገልግሎት አሁን ላይ የዲላ ዩኒቨርሲቲ በማቅረቡ ከፍተኛ ኪሳራ አስቀርቶልናል ብለዋል፡፡