የዲላ ዩኒቨርሲቲ ከ134 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ግብዓት ለአማኑኤል አረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ድጋፍ አደረገ።

ዲዩ ነሐሴ 04/2013 ዓ.ም (ህ.ግ) የሀገር ባለውለታ የሆኑትን አረጋውያንን መንከባከብ የእያንዳዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን የገለጹት የዲላ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና አጋርነት ዳይሬክተር አቶ ክብሩ አለሙ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ የማህበረሰብ አገልግሎት አጋርነት እንደሆነ ገልጸው ወደፊትም ይህን መሰሉ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር አለማየሁ አካሉ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ኘሬዝዳንት ጽ/ቤት ኃላፊና የድጋፍ አስተባባሪዎች ቡድን መሪ በበኩላቸው የሀገር ሀብት የሆኑትን አባቶች እና መንከባከብ የዚህ ትውልድ ኃላፍነት እንደሆነ ተናግረው ወጣቱ አባቶቹን እንዲጎበኝና እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ አብነት አየለ የአማኑኤል አረጋውያን ማዕከል መስራች እና ስራ አስኪያጅ ዩኒቨርሲቲው በተቸገሩበት ወቅት ያደረገላቸው ድጋፍ አረጋውያንን እየተንከባከበ ላለው ማዕከል ችግሮችን የሚቀርፍ እንደሆነ ተናግረዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው አረጋውያን መካከል አቶ አየለ ወ/ጊዮርጊስ እና ወ/ሮ ብዙነሽ ባሊ በበኩላቸው በተደረገላቸው ድጋፍ እጅጉን መደሰታቸውን ገልፀው ወደፊትም ይህ አይነቱ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሌሎች አካላት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል ።